ጳጉሜ ማለት ምን ማለት ነው ❓
ጳጉሜ ወርን ለምን እንጾማለን ❓
ለምንስ እንጠመቃለን ❓
ጻጉሜ ሦስት ርኅወተ ሰማይ ነው፣ ሰባቱ ሰማያት ይከፈታሉ ጸሎታችን በሙሉ ያርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ አገራችን ዘመን አቆጣጠር የጳጉሜ 13ኛ ወር ተብላ ትቆጠራለች። ወርሃ ጳጉሜ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 13ኛ ወር ተብላ ትቆጠር እንጂ በእለት ወይም በቀናት ብዛት ግን 30 ቀን ልትሞላ ቀርቶ ከአንድ ሳምንት እንኳን ያነሰ የቁጥር ብዛት የያዘች ወር ናት። በ3ቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ መግቢያ ላይ 5 ቀን ስትሆን በዘመነ ዮሐንስ መጀመሪያ ላይ ማለትም በ4ቱ ዘመናት ውስጥ በ 1 ዘመን ብቻ 6 ቀን ሆና ትቆጠራለች።
✍ጳጉሜን ለምን እንጾማለን ?
የጳጉሜ ወር በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ወር ተደርጋ ትታሰባለች፣ ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ፤ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው እና የሚያልፍበት እንደ ሆነ ሁሉ ዳግም ምጽዓትም ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከጊዜያው ወደ ዘላዓለማዊ መሻጋገሪያ ስለሆነ ነው ጳጉሜ የእለተ ምጽአት ምሳሌ የሆነችው፡፡
በዚህም ምክንያት የኦርቶዶክስ አማኞች የጳጉሜን ወር በሱባኤ፣ በጾም፣ በጸሎት ያሳልፋሉ በገዳም ያሉ አባቶች ጳጉሜን በዝግ ሱባኤ ያሳልፋሉ በእርግጥ ጳጉሜ ከሰባቱ አጽዋማት ውስጥ ባትካተትም፤ ጳጉሜን በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ብንጾም የበረታን፣ ሱባኤ ብንይዝባት፣ የቻልን በተዐቅቦ ብናሳልፋት ትልቅ ጥቅም እናገኝበታለን።
አንደኛ በፈቃዳችን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በሱባኤ ብናሳልፍ ፀጋና በረከት ያሰጠናል፣ ሁለተኛው ጳጉሜ የአዲስ ዓመት መቀበያ የዋዜማ ቀናት በመሆኗ አዲሱን ዓመት በጾም፣ በጸሎት በሱባኤ ብንቀበል አዲሱ ዓመት የበረከት፣ የረድኤት ይሆንልናል ማለት ነው፡፡
አዲሱን ዓመት በተለይም በዋዜማው በጸሎት ብንቀበል አዲሱ ዓመት የበረከት ዓመት፣ ያሰብነውን ያቀድነውን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሳካበት ይሆንልናል፣ የገዳም አባቶቻችን የጳጉሜን ወር መንፈሳዊ ጥቅም ስለሚያውቁ በፈቃዳቸው በታላቅ ሱባኤ ሆነው ስለ አገር፣ ስለ መጪው አዲስ ዓመት መልካምነት ፈጣሪን ይማጸኑበታል፣ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነንና እነሱ የሄዱበትን መንገድ ተከትለን እንደ እነሱ ልንጠቀም ያስፈልጋልና ወርሐ ጳጉሜን በጾም፣ በጸሎትና ፣ በሱባኤ ብናሳልፍ እንጠቀማለን፡፡
እግዚአብሔር እንዲታረቀን፣ ምሕረቱን እንዲመልስልን፣ ወረርሽኙን እንዲያጠፋልን፣ ለቅድስት ቤተ ክርስትያናችንና ለአገራችን ሰላም እና አንድነት እንዲሰጥልን ወርሐ ጳጉሜን እንደ በፊቱ በመብላት በመጠጣት ሳይሆን በጾም በጸሎት ብናሳልፍ ጥቅሙ ለእኛው ነው፡፡
👉ጳጉሜን ለምን እንጠመቃለን ?
እንደሚታወቀው ብዙዎቻችን ወርኃ ጳጉሜን እንጠመቃለን፣ ጳጉሜን የምንጠመቅበት ዋናው ምክንያት ከሊቀ መልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ጋር የተያያዘ ነው፣በዚህ በጳጉሜ ወር በዓለም ላይ ያሉ ውቅያኖሶች፣ ባህሮች፣ ወንዞች፣ ኩሬዎች ጸበሎች በአጠቃላይ ሰማይ ተከፍቶ ውኃዎች በመላክእት የሚባረኩበት ስለሆነ፣ ጳጉሜን የቻልን ጸበል ቦታ ሄደን፣ ወይም በአከባቢያችን ጸበል ካለ እዛም ሄደን፣ መሄድ ባይመቸን፣ ቤታችን ውስጥ ባለው ውኃ ብንጠመቅ እንባረክበታለን ከበሽታችንም እንድንበታለን፡፡
በጳጉሜ ጸበል፣ እንኳን የሰው በሽታ፤ በሽታ ያለው እህል፣ በሽታው ይለቀዋል፣ ገበሬው ከጳጉሜ ወዲያ ነው የሚጠፋውንና የማይጠፋውን እህል የሚለየው፣ በተለይም ጳጉሜ ሦስት፣ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በአሉ ስለሆነ፣ በዚህ ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ውኃችን የሚባርክበትና ለሰው ልጆች በፈጣሪው ፀጋ፣ ድኅነትና ፈውስ የሚያሰጥበት ቀን ስለሆነ ብንጠመቅ ከበሽታችን እንድናለን፡፡
በመፅሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራ 5 ቁጥር 4 ላይ "አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ፣ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኃላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር" ይላል፣ የጌታ መልአክ "ውኃውን ያናውጥ ነበር" የተባለው ከሰማይ ወርዶ ውኃውን ይባርከው ነበር ለማለት ነው፣ ውኃውም የሚናወጠው የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ሲባርከውና እና በመጠመቂያው፣ ለፈውስ ደጅ የሚጠኑት፣ ህሙማን ውኃው በመልአኩ መባረኩን የሚያውቁት ውኃው ሲናወጥ ነው፡፡
ዛሬም ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በዓለም ላይ ያሉትን ውሃዎች ሁሉ ስለሚባርካቸው፣ ብንጠመቅባቸው እንፈወሳለን፣ ቅዱስ ሩፋኤል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቅዱሳን መላእክትም ውኃውን ይባርኩታል ጳጉሜ ሦስት ይህ ብቻ አይደለም ሊቀ መልአኩ ያስለመደን ነገር አለ፣ ሁል ጊዜ ጳጉሜ ሦስት ሌሊት፣ ጠዋት፣ ከሰዓት ወይም ምሽት ላይ ይዘንባል፣ ይህ ከሰማይ የሆነ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸበል ነው፡፡
ጳጉሜ ሦስት በዘነበው ውኃ መጠመቅ ትልቅ መታደል እና ፈውስ ነው፣ በደዌ ይሰቃይ የነበረው ኢዮብም በዚህ ሳምንት ነው ተጠምቆ ነው የዳነው፡፡
የቅዱስ ሩፋኤል እለት የዘነው ዝናብ በዕቃ ይቀዳና ይቀመጣል፣ በተቀዳው ጸበል በውኃው እህሉ ይቦካበታል፣ ቤቱ ደጁ ይረጭበታል፣ ይህም የሚሆነው የቅዱስ ሩፋኤል እለት የዘነበው ውኃ እርኩሳን መናፍስትን ስለሚያርቅ ነው፣ በጸበሉ በረከት እህሉን ያበረክትልናል፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሦስተኛው ነው፣ በመጀመሪያዋ እለተ ፍጥረት እግዚአብሔር መቶ ነገደ መላእክት ፈጥሮ በአሥር ከተማ ሲያኖራቸው ቅዱስ ሩፋኤል ራማ ላይ ነው ከነ ሠራዊቱ ያረፈው፣ በራማም መናብርት ተብለው ለሚጠሩት አሥሩ ነገድ አለቃ ወይም መሪ ሆኖ በእግዚአብሔር ተሹሟል፣ በኋላም መጋብያን በሚባሉ በሃያ ሦስቱ ነገድ ላይ ተሹሟል፡፡
ስለዚህ ጳጉሜ ሦስት የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓሉ ነው፣
ይህንንም እራሱ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በመጽሐፈ ጦቢት ምዕራፍ 12 ቁጥር 15 ላይ "ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ" በማለት ተናግሯል፣ የስሙንም ትርጉም ስንመለከት ሩፋኤል ማለት የእግዚአብሔር ሐኪም ማለት ነው፣ ቅዱስ ሩፋኤል "ፈታሔ ማህፀን" ስለሆነ እርጉዝ የሆኑ ሴቶችም ፀበሉን በመጠጣት፣ በሰላም ይገላገላሉ፣ በሰላም ይወልዳሉ ማለት ነው።
👉የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአት እንዴት እንደሚመጣ፣ እንዴት እንደሚገለጥና እንዴት ፍርድ እንደሚሰጥ የሚጠበቀውን ቀንና የዘመን መጨረሻ ዳግም ምጽአቱ የሚነገርበት ሳምንት ስለሆነ ነው። በወርሃ ጳጉሜ እለታት በቤተክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ የሚቀርበው ስብሃተ እግዚአብሔር ሁሉ ስለነገረ ምጽአቱ ይናገራል። ጳጉሜ የወሮቹ መጨሻ፣ የሚመጣው አዲስ ዘመን ዋዜማ እግዚአብሔርም በዚህ ዘመን ይመጣል ተብሎ ከሚነገርባቸው ቀናት እና ዘመናት ወርሃ ጳጉሜ አንዷ እንደሆነች ቅዱሳት መፅሐፍት እና የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ያስተምራሉ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን 🙏🥰
Forwarded from♡የመዝሙር ግጥሞች♡

1September 5, 2026 30