አዲሱ የመረጃ ነጻነት አዋጅ እስከ 5 ዓመት እስራት የሚያስቀጡ ቅጣቶችን አካቶ ጸደቀ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር… — ኮድ 3ሜትር ትራንስፖርት አሽከርካሪ ና ባለንብረት ሲቪክ ማህበር — TG.ME

Forwarded fromTITIKVAH-ETHIOPIA
አዲሱ የመረጃ ነጻነት አዋጅ እስከ 5 ዓመት እስራት የሚያስቀጡ ቅጣቶችን አካቶ ጸደቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 1427/2018ን መርምሮ አጽድቋል።

🏢 የግል ድርጅቶች መረጃ የመስጠት ግዴታ አለባቸው

ቀደም ሲል መረጃ መጠየቅ የሚቻለው ከመንግሥት አካላት ብቻ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ማሻሻያ ግን ማንኛውም ሰው " በግል ድርጅቶች ይዞታ ሥር የሚገኝ መረጃን " ጭምር መጠየቅና ማግኘት እንዲችል ተደርጎ ሕጉ ሰፍቷል።

💵 ለጋዜጠኞች ነፃ መረጃ ፤ ለሌሎች ጠያቂዎች የማባዣ ክፍያ

መገናኛ ብዙኃን (ጋዜጠኞች) መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚሠሩ በመሆናቸው ያለምንም ክፍያ መረጃ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ሲሆን ሌሎች መረጃ ጠያቂዎች ግን ሰነዶችን ለመገልበጥ (ፎቶ ኮፒ) የሚያስፈልገውን የማባዣ ወጪ ብቻ እንዲከፍሉ ተደንግጓል።

🏗️ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ግልጽነት

ማንኛውም የመንግሥት አካል የሚተገብረውን ፕሮጀክት ፍሬ ነገር ብቻ ሳይሆን፣ የፕሮጀክቱን ዝርዝር አፈጻጸም፣ ተጠቃሚዎችን እና ያስገኘውን ውጤት መረጃ ለጠቅላላው ሕዝብ በተለያዩ የማሰራጫ ዘዴዎች ይፋ የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል።

🔍 የአካል ጉዳተኞች መብት

የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ሊነበብ፣ ሊታይ ወይም ሊደመጥ በሚችል አግባብ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ምክንያታዊ እርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለባቸው።

⚠️ እስከ 5 ዓመት እስራትና የገንዘብ ቅጣት የሚያስቀጡ ጥፋቶች

🔴 እስከ 5 ዓመት እስራት ወይም 100,000 ብር ቅጣት ፦

• መረጃን ለመከልከል በማሰብ ሆን ብሎ ሰነድን ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ፣ የደለዘ ወይም የደበቀ የሥራ ኃላፊ።
• ሙስናን፣ ሕገ-ወጥ አሠራርን ወይም የሥራ ብቃት ጉድለትን ለመሸፈን መረጃን በሚስጥር የያዘ አካል።
• የግለሰብን ወይም የድርጅትን ስም (ቅሌት) ለመሸፈን መረጃን ደብቆ የያዘ ኃላፊ።

🟠 እስከ 3 ዓመት እስራት ወይም ከ25,000 እስከ 100,000 ብር ቅጣት ፦

• ሆን ብሎ የተሳሳተ ወይም ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ለጠያቂ የሰጠ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ።
• ሚስጥር መሆኑን እያወቀ የመከላከያ እና የሀገር ደህንነት መረጃን አሳልፎ የሰጠ አካል።
• በአዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመረጃ ጠያቂዎች ከአንድ ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ምላሽ ያልሰጠ (ሲጠየቅ ችላ ያለ)።

🟡 እስከ 1 ዓመት እስራት ወይም ከ25,000 እስከ 50,000 ብር ቅጣት ፦

• የመረጃ ጥያቄን ወይም በቃል የቀረበን ጥያቄ በቅጽ ላይ ለመሙላት ፈቃደኛ ያልሆነና ግልባጩን የከለከለ።
• እያወቀ ለተቋሙ ማሳወቂያ ሐሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ የሰጠ ሠራተኛ።
• መረጃን አትሞ የማውጣት ግዴታን ያላከበረ ኃላፊ።

ምንጭ፦ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

@tikvahethiopia
June 25, 2026 305 1