ዝምታ ራሳችንን የምናይበት ጥሩ መጽሔት(መስታወት) ነው። አብዛኛውን ሰዓት በወሬ ተጠምዶ የሚውል ሰው ራሱን… — Dn Abel Kassahun Mekuria — TG.ME

ዝምታ ራሳችንን የምናይበት ጥሩ መጽሔት(መስታወት) ነው። አብዛኛውን ሰዓት በወሬ ተጠምዶ የሚውል ሰው ራሱን የሚመለከትበት እድል አይኖረውም። በሌሎች ኃጢአት ሲፈርድ፣ ሲተችና ሲያማ ስለሚውል የራሱን ስህተትና ውድቀት ለማወቅ ይቸገራል። ቀኑን ሙሉ እንዲሁ ሲያወራ የሚውል ሰው የሚያሳዝነው ዝም አለማለቱ ብቻ ሳይሆን የሚጠቅም ነገር የማይናገር መሆኑም ጭምር ነው። ነገር ግን ማር ይስሐቅ እንደሚለው "አንድ ሰው ከሰዎች ጋር ብዙ ማውራት ባቆመ ጊዜ ወደ ራሱ ይመለሳል። በእግዚአብሔርም ፊት ምግባሩን ማቅናት ይጀምራል"

የሥጋ አንደበታችንን መቆጣጠርና ዝም ማስባል ስንችል የነፍስ ጆሮአችን ንቁህ መሆን ይጀምራል። ስለዚህም ነፍሳችን ሳይሰለች ከልባችን ደጅ ቆሞ የሚያንኳኳውን የመልካሙን እረኛ ድምጽ ትሰማለች። ደጇንም ከፍታ ታስገባዋለች። ከእርሱም ጋር ለእራት ትሰየማለች።(ራእይ 3፥20) በእውነት ይህ እንደ ምን ያለ መታደል ነው? ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር "የዝምተኛ ሰው ጆሮ የእግዚአብሔርን ድንቆች ትሰማለች" ያለው ለዚህ ይሆን?!

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
[email protected]
❤103🙏21🥰8👍3
September 1, 2026 1.8K 1 21