የኖኅ መርከብ ፍጥረታትን ሁሉ ከጥፋት ውኃ ከማዳኗ ጀርባ እንዴት እነዚያን ሁሉ ግዙፋን፣ ማዕከላውያን እና… — Dn Abel Kassahun Mekuria — TG.ME

የኖኅ መርከብ ፍጥረታትን ሁሉ ከጥፋት ውኃ ከማዳኗ ጀርባ እንዴት እነዚያን ሁሉ ግዙፋን፣ ማዕከላውያን እና ቀሊላን የምድር ፍጥረታት የምትሸከም እና ለሁሉ የምትበቃ መርከብ ሆና ታነጸች የሚለው በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው።

በእርግጥ የመርከቢቱን ርዝመት፣ ወርድ እና ከፍታዋን መጥኖ እንዲህ ሥራ ያለው፤ ከእጸዋትም መርጦ “ከጎፈር እንጨት” አዘጋጅ ብሎ ያዘዘው “የፈጠራቸው እና የሚያውቃቸው አምላክ ስለሆነ” መርከቡ ባይሸከማቸውና ባይበቃቸው ነበር የምንገረመው።

ዛሬ ግን በኖኅና በልጆቹ ሳይሆን በመለኰት እጅ ስለ ታነጸችው ሕያው መርከብ፥ ወርድና ቁመቷ፣ ጎንና ስፋቷ በሰው መጠን ስለሆነው ስለምትናገረዋ ነባቢት ሐመር ድንግል ማርያም እያሰበ ኅሊናዬ ከመደነቅ አልፎ ተጨነቀ። የኖኅ መርከብ እነዚያን ፍጥረታት መሸከም እንድትችል በመጠንም፣ በስፋትም ትልቅ ሆና ነበር የታነጸችው። ድንግል ማርያም ግን ከዕብራውያን ሴቶች የተለየ ግዘፍ ሳይኖራት፣ በዓለም ያሉትን አንስት በአካል መጠን ሳትበልጣቸው በውስጧ ወርድ ቁመት፣ ላይ ታች፣ ግራ ቀኝ የሌለው፤ እንኳን የኖኅ መርከብ ዓለማት የማይወስኑትን አምላክ ተሸከመችው። ስለዚህ ድንቅ ነገር ከአባ ሕርያቆስ ጋር ሆኖ “ከስፋት ጋር የሆድ መጥበብ” እንደ ምን ያለ ነው? ብሎ ከመገረም በቀር ምን ልንል እንችላለን?

የኖኅ መርከብ ምንም ሞገድ ባይሰባብራት ውኃ ባያሰጥማትም እሳት ግን በውስጧ አልያዘችም ነበር። ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ቀሚሱ እሳት የሆነ አምላክ ያደረባት፤ መለኰታዊ ነበልባል የተሳፈረባት የማትቃጠለው መርከብ ድንግል ማርያም ናት!!!


ዲያቆን አቤል ካሣሁን
የካቲት ፫ - ፳፻፲፰ ዓ. ም.
https://t.me/Dnabel
❤199🙏19🥰9👍3🔥1
August 16, 2026 4.9K 1 27