+++ "እግዚአብሔር የጣላት እሳት" +++
በደብተራ ኦሪት በመሠዊያው ላይ የሚነደውና መሥዋዕቱ ይቃጠልበት የነበረው እሳት ከሰማይ የወረደ ነበር። ይህም እሳት ዘወትር እንዳይጠፋ የአሮን ልጆች (ካህናቱ) ማለዳ ማለዳ እንጨት እየጨመሩ እንዲያቀጣጥሉና እንዲያነዱት እግዚአብሔር አዝዟቸዋል።(ዘሌዋ 6፥12) ከማዕጠንት ጀምሮ እስከ እንስሳት በድንኳኑ የሚቀርቡ ማናቸውም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ሁሉ የሚበሉት ከሰማይ በወረደው በዚህ "የእግዚአብሔር እሳት" ነው።
ታዲያ ከእለታት በአንዱ ቀን የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እንዲህ አደረጉ። ለእግዚአብሔር የእጣን መሥዋዕት ማቅረብ ፈልገው ለየራሳው ጥናውን (ማዕጠንት) አነሡ። ነገር ግን በጥናው ውስጥ ያደረጉት ከሰማይ የወረደውን "የእግዚአብሔር እሳት" ሳይሆን፣ ከመንደር ጭረው ያመጡትን ወይም ራሳቸው ያቀጣጠሉትን "ሌላ እሳት" ነበር። በዚህም እግዚአብሔር ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት ስላቀረቡ አምላክ ተቆጣ። በፊቱም እሳት ወጥቶ እንዲበላቸው አደረገ። እነርሱም ወዲያው ሞቱ።(ዘሌ 10፥1-3) ሊቀ ካህናቱ አሮንን እየተከተሉ እንዲያገለግሉ የተመረጡት ሁለቱ ልጆቹ ገና አገልግሎታቸውን በቅጡ ሳይጀምሩ ተቀሰፋ። ለመሆኑ እነዚህ ሁለት የኦሪት ወጣት ካህናት የተቀጡበት "የሌላ እሳት" ታሪክ ለሐዲስ ኪዳኑ ዘመን ምን ምሳሌ ይኖረው ይሆን?
እግዚአብሔር በኦሪቱ ድንኳን እሳትን እንዳወረደ፣ በሐዲስ ኪዳንም የሰውን ልጅ ለማዳን ከሰማይ ሲወርድ ይዞልን የመጣው እሳት አለ። "እሳተ አምጻእኩ ለብሔር፤ ወምንተ እፈቅድ ዘእንበለ አንድዶታ" - "በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ?" እንዳለን።(ሉቃ 12፥49) ይህ መድኃኒታችን በምድር ላይ የጣለው እሳት ምንድር ነው? አገልግሎቱስ እንዴት ነው?
ጌታችን በምድር የጣላት እሳት "ወንጌል" ትባላለች። ሰው ሰውነቱን ንጹሕና የተቀደሰ ሕያውም መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብባት "የእግዚአብሔር እሳት" ወንጌል ነች። ይህች ወንጌል ጌታ አንድ ጊዜ በምድር የጣላት፣ እኛ ደግሞ ለዘወትር እንዳትጠፉ የምናቀጣጥላትና የምናነዳት እሳት ነች። የማቀጣጠያው እንጨቶችም ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እና ማንበብ ናቸው። ያለ ወንጌል እሳትነት ምንም መሥዋዕት እንድናቀርብ አልተፈቀደልንም። ነገር ግን እንደ አሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ ከመንደር ቆስቁሰን ወይም ራሳችን አቀጣጥለን የምናመጣቸው "ሌላ እሳት" የተባሉ ከንቱ ፍልስፍናዎችና እንግዳ ትምህርቶች የእግዚአብሔርን ቁጣ ይቀሰቅሱብናል።
ዳግመኛም እሳት የተባለው በጥምቀት ጊዜ በሁላችንም ላይ የወረደው ጸጋ እግዚአብሔር ነው። ይህም ጸጋ ለመዳናችን ዓይነተኛ ሚና አለው። ይሁን እንጂ ልክ በደብተራ ኦሪት እንደ ወረደው እሳት ካልተንከባከብነው እና ካላቀጣጠልነው ሊዳፈን እና የሌለ ሊመስል ይችላል። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስ "እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው...በአንተ ያለውን የእግዚአብሔርን ሥጦታ እንድታነሣሣ አሳስብሃለሁ" በማለት የሚመክረው።(2ኛ ጢሞ 1፥6) እግዚአብሔር ለሰጠን ጸጋ ማቀጣጠያዎቹ ደግሞ ጾም፣ ጸሎትና መንፈሳዊ ትሩፋት ሁሉ ናቸው። እርሱ የሰጠህን የጸጋ እሳት ከማቀጣጠል ይልቅ "ሌላ እሳት" ላምጣ ያልህ ቀን ግን ታላቅ ጥፋት ያገኝሃል።
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
156
26
4
1August 7, 2026 6.6K 44