የዘመነ ትውልድ ፤ የፋኖ መሪዎች ቀን ስለሆነ ስለአቢዮተኛውና እምቢተኛው ዘመነ፥ "የአቅምህን ያሕል አልሠራህም፣ ከአንተ የምንጠብቀው ብዙ ነው፤ ብዙ እጠብቃለሁ" ስላለኝና ስለሚለኝ ዘመነ ጥቂት ልበል !! አስኳላን የዘለቀ ፣ ታሪክን ያነበበ፣ እምነትና ፅናትን ፣ መንከራተትና መሳደድን ኖሮበታል። አንዳንዴ ደቡብ አፍሪካዊውን እምቢተኛ ማሌማን፣ አሊያም ፈረንሳዊውን Robespierreን ሊያስታውስህ ይችላል። ከብርሃኑ ነጋም ፣ ከአሳምነው ፅጌም፣ ከኮለኔል ፍፁምም፣ ከታናሾቹም ከታላቆቹም ጋር ብዙ አሳልፏል። ከብዐዴን እስከ አርበኞች ፣ ከግንቦት-7 እስከ አማራ ፋኖ በጎጃም...በየትኛውም አደረጃጀት የትግል እድልን ለመጠቀም ታትሯል። በዚህ ሁሉ ማለፍ የትግል ርሃብና ልምድ እንጂ አድርባይነትንና ጥቅመኛነትን አይገልፁም። "ምን እናርግልህ? ፣ ውጭ አገር እናመቻችልህ ፣ ድርጅት እንክፈትልህ ፣ ገንዘብ ይስተካከልልህ"... ያልቀረበለት ማማለያ የለም። እሱ እቴ !! ቀድሞ የነቃ ነው!! ዛሬ ዘመነ ፥ ልጁን ፣ ወንድሞቹን፣ አጎቶቹን ፣ ዘመዶቹን ሁሉ በትግል ያሰለፈ ፥ ከአማራ አቢዮት መሪዎች አንዱ ነው። የትግል ምዕራፎቹ ምስክርነት ይናገራል፤ ሀ) በመጀመሪያ የትግል ሰልፉ ብዙዎቻችን ሳይገባን ጠጋ ብሎ አያቸው ፣ ተረዳቸው፣ አይሆኑም። እናም ዱር ቤቴ አለ። ከአስመራ እስከ ካምፓላ ወቅት የፈጠራቸውን አደረጃጀቶች ተከትሎ ባዘነ። ለ) ቀጥሎ የነቃ የበቃ ወጣት እንዲፈጠር ቀሰቀሰ። ዘመነ የጎጃም ወጣትን ቀስቅሷል፣ አንቅቷል፣ አደራጅቷል፣ ድርጅት ፈጥሯል ፣ ወጥነት ያለው በተማከለ መዋቅራዊ ቁጥጥር ስር የታቀፈ የፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ወታደራዊ መዋቅር ፈጥሯል። ሐ) ዛሬ ከጓዶቹ ጋር ድርጅት ፈጠረ። የአማራ ሕዝባዊ ኃይልን ከጓዶቹ ጋር አደራጀ። አሳደገ፣ አሰፋ ፡ ታላቅ ድል አድራጊ ሠራዊት፣ የፖለቲካና አስተዳደራዊ መዋቅር የዘረጋው "የአማራ ፋኖ በጎጃም" ተወለደ። የዘመነ የቀደሙ ፍላጎቶችና ልፋቶች ሁሉ፡ በዚህ ምዕራፍ አንድ ከተቋጩ፣ ቀጣዮቹ ምዕራፎች ገና ብዙ ሥራ ፈላጊ በመሆናቸው ብርቱ እውቀትና ጉልበት ፈላጊ ናቸው። ዘመነ በግልም በቡድንም ተፈትኗል፥ ይፈተናል፤ ዘመነ ተሳዷል ፣ ታስሯል ፣ ስንቱን የግድያ ሙከራ አምልጧል። የትውልድ ቀዬው መርዓዊ ነዋሪዎች በፋሽስቶች የቤት ለቤት ጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጅተዋል። ይሕ በአንዲት ጠባብ የወረዳ ከተማ ለኖረ ቤተሰቡና ቤተዘመዱ በሚገኙበት የተፈፀመ ግፍ ለአንድ ታጋይ ምን ማለት ይሆን!? ፤ ጓዶቹ ያውቃሉ። ንግግሮቹ ለትርጉም ፣ ድርጊቶቹ ለስላቅ ሳይዳረግ እዚህ አልደረሰም። ወደፊት ያለው ይብሳል !! "ሰነፍ ነው" የሚሉት እንዳሉ "አርበኛ ጀግና ነው" የሚሉት ሞልተዋል። "ነፃ አውጪ ነው የሚሉት እንዳሉ "አስገዳይ ነው" የሚሉት አልታጡም። "የስልጣን ጥመኛ" የሚሉት እንዳሉት ሁሉ "ራሱን ለሕዝብ የሰጠ" የሚሉት አሉ። ሌላው ቀርቶ በአካሉ ሙላት ታጋይነቱን ሊነጥቁት የሚከጅላቸው አልታጡም። የሕልውና አደጋቸውን ዘመነ ፤ የሕልውና ትግላቸውን በዘመነ ላይ ያደረጉ ማየት ቢያሳዝንም የሒደቶች አካል ነው። ከአደራጀው ተቋም ጓዶቹ ጋር መሻከር ተፈጥሯዊ ነውና አይጠፋም፣ ከሌሎች የፋኖ አደረጃጀት ጓዶቹ መካከል ከአንዳንዶች መፎካከር የትግል ደንብ ነው፣ አማራን ሳይሆን ኢትዮጵያን ከሚሉ ትችትና ዘለፋ ቀጥሏል፣ እምቢተኛ ታጋይ ኃይል ያደራጀባቸው የገዢ ቡድኖች ሊያጠፉት እንቅልፍ ማጣታቸው የሠርክ ተልዕኳቸው ነው። ሌላው ይቅርና የሚቃረኑት ብቻ ሳይሆኑ በጭፍን የሚያወድሱት ፥ እሱን ለማወደስ የሚሔዱበት ርቀት፣ እሱን ለመከላከል ተቺዎችን የሚዘልፉበት መንገድ ሁሌም አወንታዊ አይደለም። "ለመውደድ ሲሉ ጠላትና ኮናኝ የሚያራቡ ደጋፊዎቹ ቀላል አይደሉም። የተቋም ግንባታ ፈተናዎች ውስጥ የታለፉም የሚቀጥሉም አሉ፤ የጎጃምን ፋኖና አደረጃጀት የመከፋፈልና የመበተን ብርቱ ጥረት ታልፏል !! ➩ መጀመሪያ የአማራ ሕዝባዊ ኃይልን የማጥፋት/የመከለስና የመበረዝ አላማ ከሸፈ። ➩ በመቀጠል በዕዝና ሕዝባዊ ኃይል መካከል ንቃቃት ፈልጎ የመበተን አላማ ከሸፈ። ግን! "የድማማ ስምምነት" አደረጃጀቱን ፖለቲካ-መር እንዲሆን አድርጎ ደምድሞታል። ➩ በጎጃም ሌላ ወታደራዊ ዕዝ የመፍጠር አላማ አልተሳካም። ➩ በቅርብ አንድ አማራዊ መዋቅር በመፍጠር ሒደት የመጣ ማሳነስና መግፋት አልተሳካም። ትግሉን እና የፋኖ አንድነት መሰናክሎችን የሁለት ሰዎች ፉክክር የማስመሰል ትርክቱ ነገሩን ያለማጤን (False equivalence) ሆኖ ማጠልሸቱ ቀጥሏል። ለምን!? የሚለውን ጊዜ ይፍታው። ዘመነ ከጎጃም አለፍ፡ ፋኖነትን ከስርዓቱ ጋር በመነጠጠል የበኩሉን ሚና ተወጥቷል። ከመቶ ጊዜ በላይ ድሮን ተጥሎበት የማይናወጥ ወጥ መዋቅራዊ ቁጥጥር ያለው አንድ ኃይል የፈጠረ ነው። ዘመነን ጠልቶ የሠራውን ድርጅት መውደድ እንዴት ያለ ነው!?፤ የጎጃምን ፋኖ እንወዳለን ፥ ገድሉን እናደንቃለን፥ ነገር ግን ዘመነን አንፈልግም የሚሉ ጥቂት አይደሉም። የተዘነጋው ነገር ፦ ዘመነ የገነባው መዋቅርና ሠራዊት መሪዬ ብሎ ተቀብሎታል። መሪዎቹንና ድርጅቱን የሚቀበል፣ የሚያከብር፣ የሚጠብቅ መዋቅር ተፈጥሯል። ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ቁጥጥር ስር ያለው የጎጃም ሕዝብ መሪዬ ብሎታል። እናስ? ፥ ዘመነን ጠልተህ እንዴት ይሆናል? በመውጫዬ ፥ ዘመነ የመሪነት ተክለ ቁመናው ጉድለት አያጣውም። ፎቶ ሲደረድር ፖፑሊስት ሆኖ ይታየኛል !! ርቱዕ አንደበቱ ስሜታዊ ሲሆንና ስል አንደበቱ ኢ-ፖለቲካዊ ሲሆኑ ደስ አይለኝም። በእውቀት ፍለጋ የሰነድ ስራ ፣ በስልጠና ፣ በድርጅት መዋቅር ቁጥጥር ረፍት የለሽ ስራ ስለምጠብቅ ለትንሽ ትልቁ ጉዳይ እሱ ብቅ ብሎ ሲናገር ደስ አይለኝም። ራሱን የትኩረት ማዕከል ሲያደርግና "እኔ" ብሎ ሲናገር ፤ ነገሮችን ከእሱ ጋር ሲያያይዛቸው ምቾት አይሰማኝም። በዚህ ሁሉ መሐል ብዙ ብዙ ዘመነዎች ተፈጥረዋል!! ብዙ ጀግኖችና አርበኞች ተሰልፈዋል። አንድ ታጋይ ትልቁ ስኬቱ የሚተኩትን ብቻ ሳይሆን የሚበልጡትን ታጋዮች ማሰለፍ መቻሉ ነው። ዛሬ የጎጃም ትግል ከዘመነ በላይ ነው፤ የሌሎችም አማራ ፋኖ መሪወች ትግል ከመሪ ግለሰቦች በላይ ነው። ከሁሉም ሕዝብ ይቀድማል፣ በመቀጠል ድርጅትና መዋቅር ይበልጣል፣ ከዚያም የቡድን አሠራር እና ጓዳዊነት ከራስ በላይ ነው። በዚህ መሐል የበለጠ መስከን፣ የበለጠ መጠንቀቅ፣ የላቀ የፖለቲካና ትግል እውቀት ትጥቅ አስፈላጊ ነው። ትግሉ የጉልበት/ብረት ብቻ አይደለም። ትግሉ ያለ እውቀት፣ ያለማስተዋል ፣ ያለ ፖለቲካ የሚሆን አይደለምና የላቀ ፖለቲካዊነትን ይፈልጋል። የተጀመረ እንጂ ያለቀ ትግል የለም። የበለጠው የወደፊቱ ነው!! [ማስታወሻ፥ መሠል የትግል መሪነት ምስክርነት የሚገባቸው የአማራ ልጆች በየስፍራው አሉ። ጊዜ ሲፈቅድ እንናገራለን።]
የዘመነ ትውልድ ፤ የፋኖ መሪዎች ቀን ስለሆነ ስለአቢዮተኛውና እምቢተኛው ዘመነ፥ "የአቅምህን ያሕል… — ራስ አማራ|Ras se'ela kirstos — TG.ME
September 9, 2024 2.4K