የቴዲ አፍሮ “ዳስ ጣል” ጥበብ ንግግር ሊገልጸው የማይችለውን ጥልቅ የሕዝብ ሕመም የመግለጽ መለኮታዊ ኃይል… — ❤️City of life❤️ — TG.ME

📌የቴዲ አፍሮ “ዳስ ጣል” ጥበብ ንግግር ሊገልጸው የማይችለውን ጥልቅ የሕዝብ ሕመም የመግለጽ መለኮታዊ ኃይል አላት። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ዳስ ጣል” በሚለው አዲስ ነጠላ ዜማው፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የተጋረደውን የሀዘን ድባብ፣ የተሰበረውን አንድነትና የጠፋውን የፍትሕ ጩኸት በሚቀሰቅስ መልኩ ተቀኝቶታል። ይህ ስራ ዝም ብሎ ሙዚቃ ሳይሆን፣ የቆሰለ ሕዝብ በራሱ ዜማ የሚያለቅስበት፣ የሚሞግትበትና ማንነቱን ዳግም የሚያውጅበት የታሪክ አካል ነው። “ሰው አይችልህ ደርሶ... ሀገር የሞተበት የት ያለቅሳል ሄዶ?” የሚለው መክፈቻ፣ የግል ሀዘንና የሀገር ሀዘን ያላቸውን ልዩነት ያሳያል። ሰው ለግል ጉዳዩ ማልቀሻ ቦታ አይጠፋውም፤ ሀገር ስትፈርስና ሕልውናዋ አደጋ ላይ ሲወድቅ ግን ለቅሶው የሚቆምበትም ሆነ የሚረግጥበት መሬት ባዶ እንደሚሆን ይነግረናል። አክሱምና ላሊበላን በአንድ አለት ያጸና የታሪክ ሰንሰለት እያለን፣ ዛሬ ሀገር ለመራመድ መቸገሯን ሲገልጽ “ምሰሶው ዘመመ ጣራውም ያፈሳል ሀገር የሞተበት የት ሄዶ ያለቅሳል" በመቀጠልም "ያቆምኳትን ሰንደቅ ተፈትኜ በእሳት እንዴት አቀርቅሬ ባንዲራዬን ላንሳት" ይለናል ። “አባይ ለዘዴው በአፍ ይቀድማል፣ አምኖ መከዳት እንዴት ያማል!” የሚለው ደግሞ፣ ሕዝቡ ለውጥና ሰላምን ተስፋ አድርጎ የሰጠውን እምነት፣ በምትኩ ግን መገለልና ክህደት ሲገጥመው የሚሰማውን የታላቅ ቁጭት መግለጫ ነው። ወርቅ አበድሮ አለት እንደመቀበል ያለ መከዳት በዝምታ የማይታለፍ ሕመም መሆኑን ይሞግታል። ቴዲ ከለቅሶ ወደ ቆራጥነት ይሸጋገራል። “መች ከሀገር ይበልጣል እኔስ አንድ ነፍሴ” በሚለው ስንኝ፣ የሀገር ሕልውና ከግል ሕይወት በላይ መሆኑን እያወጀ፣ ለታሪክና ለማንነት የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ያሳያል። “ምጥ አታስተምር ልጅ እናቷን” በማለት የሰጠው ምላሽ፣ የኢትዮጵያዊነትን ምንነት ማንም ሊያስተምረን እንደማይችልና ማንነታችን በደማችን ውስጥ ያለ ሕያው እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። “ባንዲራየን አንሳው” የሚለው ተደጋጋሚ ጥሪው ደግሞ፣ የተረገጠውን ክብር፣ የታሪክ አሻራንና ማንነት ዳግም የማስመለስ የነፃነት አዋጅ ነው። በአጠቃላይ “ዳስ ጣል” የኢትዮጵያ ወቅታዊ ነጸብራቅ ነው። ይህ ስራ ለሀገር ለቅሶ ብቻ ሳይሆን፣ የተኙትን የሚቀሰቅስ፣ የተገፉትን የሚያጽናና እና በእውነት ላይ የቆመ ትውልድ ማንነቱን ዳግም እንዲያነሳ የሚያደርግ የጥበብ ክንድ ነው። ኢትዮጵያ አመስግናለች።

April 16, 2026 358 1