በ140 ብር መነሻ መዋጮ የተጀመረው አሚጎስ የቁጠባና ብድር ማህበር ሀብቱ 10 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ
ማህበሩ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበራት ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን ከወረቀት ነፃ የስማርት አገልግሎት ማዕከል አስመርቋል።
አዲሱ የስማርት አገልግሎት ማዕከል የአባልነት ምዝገባን ማከናወን፣ መረጃ መጠየቅ፣ የብድር ሂደትን መከታተልና አስፈላጊ ሰነዶችን ማሟላት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።ማህበሩ የአባላቱን ተደራሽነትና የአገልግሎት ፍጥነት ለማሻሻል ከሚያቀርባቸው ዲጂታል አገልግሎቶች መካከል ኮር ባንኪንግ፣ ዌብ ቤዝድ ሰርቪስና የሞባይል መተግበሪያ ይገኙበታል።
አሚጎስ በመጀመሪያ በሶስት ጓደኛሞች 140 ብር መዋጮ የተጀመረ ሲሆን በ2005 ዓ.ም ደግሞ በ20 አባላትና በ9 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ተመስርቶ የቤት ለቤት የቁጠባና የብድር አገልግሎት ጀምሯል።
በ13 ዓመታት የሥራ ጉዞው ከ20 ሺህ በላይ አባላትን ማፍራቱንና እስካሁን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለአባላቱ መስጠቱን የአሚጎስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ወ/አማኑኤል ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።ማህበሩ በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ በማግኘት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች 28 ቅርንጫፎችን ከፍቶ እየሰራ ሲሆን በቀጣይ ወራት ተጨማሪ 23 ቅርንጫፎችን ለመክፈት እየተሰራ ነው ።
ከቁጠባና ብድር አገልግሎቱ ባሻገር፣ ማህበሩ ለባለአክሲዮን አባላቱ ባለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ከ50 በመቶ በላይ ትርፍ ማከፋፈሉን ገልጿል።በማህበራዊ ኃላፊነት በኩልም በከተማ ልማት፣ በበጎ አድራጎትና በተለያዩ ማህበራዊ ሥራዎች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የአሚጎስ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳዊት ወ/አማኑኤል ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
ሳምራዊት ስዩም
#ዳጉ_ጆርናል





















