የላምሮት አደባባይ( እውነተኛ ታሪክ )👩⏳🎓💔🌸 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ጊቢ( አሪድ ) መግቢያ በር… — ALAJE TIMES — TG.ME

የላምሮት አደባባይ( እውነተኛ ታሪክ )👩⏳🎓💔🌸 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ጊቢ( አሪድ ) መግቢያ በር ላይ:- የፍሬሽ ተማሪ ወጉ ደርሶኝ ከትውልድ ከተማዬ ሸገር 783 ኪ.ሜ እርቄ እራሴን አገኘሁት ! ከቤተሰብ ፣ ከጓደኛ ከለመድኳቸው ልማዶቼ ሁሉ አሁን እርቄያለሁ ! 18 አመት ያልሞላኝ ጎረምሳ ህይወትን በአዲስ መልክ ላያት መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋና በር ላይ ሻንጣዎቼን እየገፋሁ ተገኘሁ ። እንደኔው ፍሬሽ የሆኑ ተማሪዎች በሰልፍ ሻንጣቸውን እያስፈተሹ ወደጊቢው ይገባሉ ! ለፍተሻ ወረፋዬን እየጠበኩኝ እያለ ከመግቢያው በር ወደ ግራ ስመለከት አንድ በድንጋይ መሰል ነገር የተቀረጸ ሃውልት ትኩረቴን ሳበው ። ሻንጣዬን ባለበት ትቼ ሃውልቱን ጠጋ ብዬ አየሁት ! አንድ ጽሁፍ ብቻ እላዩ ላይ አየሁ ! " ላምሮት አደባባይ " ይላል ጽሁፉ ! ሃውልቱ በሴት ቅርጽ የተሰራ ነው ! ሌላ ሃውልቱን ገላጭ ነገር ግን አጣሁበት ! ....የምን ሃውልት ይሆን ? ...ወረፋ ደርሶኝ ሻንጣዬን አስፈትሼ ወደ ጊቢው ቅጥር ገባሁ ! በዚህችው ቅጽበት " ሀ " ብዬ ኑሮን በመቀሌ ዩኒቨርስቲን ጀመርኩት ! ....... ቀን አንድ ...... ህይወት ግን ይቀጥላል አይገርምምም ? ከቤቴና ከቤተሰቤ እርቄ ኑሮዬን ከተለያየ የኢትዮጲያ ክፍል ከመጡ ጎረምሶች ጋር አደረኩ ። ሁሉ ብርቁ ነበርኩኝ :- እዛው በዛው ወዳጆች አፈራሁ ። ቀን ቀንን ቆጠረ :- አይገርምም ፍሬሽ ጦ'ጣ እንዳልተባልን ፣ ግዜ ጌታ ከአዲስ ተማሪነት ወደ አሮጌ ተማሪነት ቀየረን ። አንደኛ አመት አልፎ ወደ ሁለት ሶስት እያለ :- በዛች አጭር ግዜ ስንቱን አየነው ? ይገርመኛል ሳስበው ያንን ግዜ :- ትኩስ ወጣትነት :- ልበ ሙሉነት ፣ ደፋርነት :- ምን ይሉኝን አለመፍራት :- ከፍታ ዝቅታ ብቻ ብዙ ብዙ የማይረሱ ትዝታዎች ። ህይወት ተፈተነ .... ብዙ ብዙ በህይወቴ ሆነ .....እዛ ጊቢ ውስጥ እራ'ሴን ለማጥፋት ሁሉ ሚያስመኝ ግዜ አሳልፌያለሁ አይገርምም ? አይ ልጅነት ። እና ደሞ በደስታ ጮቤ የረገጥኩበትም ግዜ ብዙ ነበር በመቀሌ ካምፓስ ቆይታዬ ....ብዙ ውርቅ የሆኑ የልብ ወዳጆች አፈራሁ .... የቅርቤ ያልኳቸውንም እሩቅ አደረገብኝ የጊቢ ህይወት ..... ምን ያልሞከርኩት ነገር ነበር ? .....ብቻ ግን አንዱ አንዱን እየተካ ፣ ግዜ እየነጎደ " ሀ "ብዬ እንደጀመርኩ መመረቂያዬ ቀን ደረሰ ! አይገርምም ጊቢ ስገባ ከቤተሰብ መራቅ ሞ'ት መስሎ ነበር የተሰማኝ ። በጣም የገረመኝ ደሞ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ቤቴ ልሄድ መሆኑን ሳውቅ :- ድጋሚ ባዶነት ተሰማኝ ። ምክኒያቱም የጊቢ ህይወት እስኪለመድ እንጂ ከተለመደ በኻላ ለመላቀቅ ፈተና ነው :- ከህይወት ጋር ተዋህዷልና መቼም በቀላሉ አይወጣም ። ለአመታት እንደወንድምና እህት ጓደኛ አብሮ ካሳለፉት ጀማ ጋር መራራቅ ህመም አለውና ። ብቻ የቁርጥ ቀኑ መጣ :- ልንመረቅ አንድ ቀን ቀረን :- እንኳን ደስ አላችሁ ሊባልልን ሃያ አራት ሰአት ማይሞላ ግዜ ብቻ ። ጊቢ ቀይረን አዲሃቂ ካንፓስ የገባን ቢሆንም ባጋጣሚ ወደ ዋናው ጊቢ በጉዳይ ሄድኩኝ :- እናም የመጀመሪያ ቀን ዩኒቨርስቲውን ስረግጥ ሻንጣ እየጎተትኩ የተገኘሁበት እዛ ቦታ ሄጄ ቁጭ አልኩኝ ! ላምሮት አደባባይ ጋር ። የካንፓስ ቆይታዬን ልመዝነው ..... ትዝታዬን ልቋጨው ልሰናበተው ። ላምሮት አደባባይ ግን ምንድን ነው ? አሁን አዲስ ተማሪ አይደለሁም ! ልመረቅ አንድ ቀን ነው የቀረኝ ስለ ላምሮት አደባባይ :- ከኔ የቀደሙት የነገሩኝን ብጥስጣሽ ታሪክ ቀጣጥዬ ማውራት እችላለሁ ! በእርግጥ በጊቢ ታሪክ ወሬ በቅብብሎሽ ነው ከድሮ ተማሪዎች እንደ አፈ ታሪክ እየተቀጣጠለ ሚደርሰው :- ላምሮት የኛ ግዜ ተማሪ አይደለችም :- በአመታት ምትቀድመን የነበረች ተማሪ ናት ። ስለዚህም በዛ ግዜ የነበሩ ተማሪዎች የነገሩን ታሪክ ተዋርሶ እኛ ጋር ደርሷል ። ላምሮት ማናት ? ለምንስ በስሟ ሃውልት ተሰራላት ? ቀደምት ተማሪዎች እንደወረደ እንዲህ ነው የነገሩን ። ላምሮት :- ሰቃይ ( ጂኒየስ ) ተማሪ ነበረች አሉ ። እዚሁ ዋናው የዩንቨርሲቲው ጊቢ ( አሪድ ) ትማር ነበር ! ቆንጆና ተግባቢም ናት እንደሰማሁት ! አንድ አስተማሪ እንደውም ወደድ'ኩሽ ከነፍኩ'ልሽ :- ፍቅሬን ተቀብለሽ :- እሺ ካላልሽኝ ውጤ'ትሽን አበላሸ'ዋለሁ ምናምን እያለ ያማ'ርራት ነበር አሉ ! ይሄን ተቋቁማ ለአራት ይሁን ለአምስት አመት ተምራ የምርቃቷ ቀን ወደ አዳራሽ ለመሄድ እየተዘገጃጀች የጋወኗ ቁልፍ በስርአት አልገጥም ብሏት :- ለጋወኗ ማያያዣ መርፌ ቁልፍ ልትገዛ ( የቀደሙት እንዳሉኝ) ጋወኗን እንዳደረገች፣ መነሳንሷን ከአናቷ ደፍታው ከዋናው ጊቢ በር አስፓልቱን ተሻግሮ ወዳለ ሱቅ እየሄደች ድንገት መኪና ገጭ'ቷት ለአመታት የተማረችበት በር ላይ ህይወቷን አጣች .... አይገርምም ? ይህቺ ልጅ ላምሮት ትባላለች ! አያሳዝንም ታሪኳ ? ያ ሁሉ እሩጫዋ ፣ ያ ሁሉ መባከኗ ስንቱን የሆነችለት ደ'ም እንባ ያለቀሰችለት ትምህርት ለካንስ እዚህ ድረስ ነበር ውሉ !!!! ቤተሰቦቿ ሊያስመርቋት ተሰብስበው መተው የልጃቸውን ሬ'ሳ ይዘው ተመለሱ ...እናም እላችኻለሁ ቀደምት ተማሪዎች እንደነገሩን :- የላምሮት ታሪክ ይሄው ነው ! ...... ዩንቨርስቲውም ለመታሰቢያ ሃውልት በሩ ላይ አሰራላት ! ዋናው ጊቢ በር ላይ ! ሁሉም ሰው ሲወጣ ሲገባ ሃውልቷን ያየዋል ። ቦታውም በተለምዶ ላምሮት አደባባይ ተባለ ። እኔም ለአመታት ከተማርኩት ትምህርት ይልቅ የላምሮት ታሪክ በብዙ አስተማረኝ ! ምን ተማርኩ ? ህይወት አጭር ናት የምወዳችሁ ! ጤዛ ነው አይተነው እያለ :- ወይም እያየነው ድንገት ሙሽሽ ስልብ የሚል ጉም ነው ! ይሄ ገባኝ ! ብዙ የለፋንለት ፣ ተጠንቅቀን የገነባነው እንደ እንቧይ ካብ ድንገት ሊናድ ይችላል ። ከሰማይ በታች አዲስ ነገር ወፍ የለችም እዚህ ምድር ላይ !ሁሉም ነገር ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው :- ንፋስንም እንደመከተል ነው ። .... ሰዎችዬ አዲስ ቀን ሲሰፈርልን :- ለመልካምነት እንዘርጋ ሌላው ሁሉ የምድር ጌጥ እረጋፊ ነው ! መልካምነት ያስጊጠን ! በእያንዳንዱ እርምጃችን :- ተቆጥሮ በተሰጠን ትንፋሽ :- የቀናውን ፣ ያማረውን ፣ ሰው ሰው ሚሸተውን ወርቅ እንቁ የሆነውን መልካሙን ስብእናችንን ኖረነው እንለፍ ። የሰው ልጅ በቀጣዩ ሰከንድ ምን እንደሚገጥመው ማያውቅ ምስኪን ፍጥረት ነውና :- ሰው ሆነን እንለፍ ። በመልካምነት ምንወሳ እንሁን :- መልካም እሁድ ። እንደጀማሪ ሰባኪ ምክር አበዛሁ አ ? አፉ በሉኝ ። ✒️ጽሁፍ ✍️ Sami Fanta ( ላይክ ፣ ኮመንት ፣ሼር እንዳይረሳ 💛💛💛 ) 🍿#ሼር #ሼር #በማረግ_ተባበሩን

September 6, 2025 1.1K 1