ያልተጀመረ ሕይወት!
“ሕይወቴ ያልፋል ብለህ አትፍራ፣ ይልቁንስ ሕይወትን ሳልጀምራት ላልፍ ነው ብለህ ፍራ” - John Henry
ሕይወት የሚያምርባት ስንኖራት ነው፡፡ ሕይወት የምትጣፍጠው ዓላማችንና የምንፈልገውን አውቀን ወደዚያ ስንንቀሳቀስ ነው፡፡ ሕይወት የምታጓጓን ከእኛ ለየት ያሉ አዳዲስ ሰዎችን ስንተዋወቅ ነው፡፡
ሕይወት የምታሳድገን ከዚህ በፊት ያልተሞከሩ ነገሮችን ለመሞከር ስንወጣ ነው፡፡ ሕይወት አዲስ ነገር የምታስተዋውቀን ከእድሜያችን ጋር አብሮ የሚመጣውን ለውጥ በማስተናገድ ወደ አዲሰ ምእራፍ ለመግባት ስንደፍር ነው፡፡ ሕይወት የምታሻግረን መዝለል ያለብንን ገደል ጥበብና ጥንቃቄ በተሞላበት ድፍረት ስንዘል ነው . . . ፡፡
በአጭሩ ሕይወት የተሰጠን አዳዲስ ነገሮችን እያደፈርንና እያጣጣምን እንድኖረው ነው! የዚህ አስገራሚ የሕይወት
ጣእምና ትርጉም የሚጠፋብንና ሕይወትን ሳንጀምራት የምናልፈው ከአንድ ነገር የተነሳ ነው፡-
1. አዲስ ነገር ስንፈራ (Fear of new things)! - አዲስ ነገርን የሚፈራ ሰው ለውጥን አጥቆ ይሸሻል፡፡ ያለበትንና የለመደውን ሲደጋግም ስልቹና የማያድግ ሕይወትን እንደኖረ ያልፋል፡፡
2. የማይታወቀውን ነገር መፍራት (Fear of the unknown)! - አዳዲስ ነገር መጀመር የሚያመጣውን ያልለመድነውንና የማይታወቀውን ሁኔታ ስንፈራ ዓለም ጥላን ሄዳ እኛ ግን ባለንበት እንረግጣለን፡፡
አስቡት እስቲ! አዳዲስ ነገሮችን ከመጋፈጥ ውጪ አንድም ቀን ውለንና አድረን አናውቀም፡፡ በየጠዋቱ አዲስን ቀን እንጋፈጣለን፣ በየስፍራው አዲስን ሰው እንተዋወቃለን፣ በየእድሜ ደረጃችን አዲስ ነገሮችን እንጋፋለን . . . ! ይህ ፈጽሞ ልንሽረው የማንችለው የሕይወት ሃቅ ነው፡፡ አዲስን ነገር ከመጋፈጥ የማያመልጠውን ይህንን ሕይወታችን ለአዳዲስ ነገሮች ክፍት በመሆን ካላገዝነው ሕይወትን ሳንጀምራት እናልፋለን፡፡
አሁን ላለንበት እድሜና ያለንበት የሕይወት ምእራፍ ላቀረበልን አዲስ እድል የሚመጥንን እርምጃ ለመውሰድ አንፍራ፡፡ ትርፍና ኪሳራህን የማስላቱን የቤት ስራችንን በሚገባ ከሰራን በኋላ ወቅቱ ወደሚጠይቅህ አዲስ ነገር ለመዝለቅ ቆርጠን እንነሳ፡፡ ሕይወትን ከፍርሃት የተነሳ ቁጭ ብለን አናሳልፋት! በፍርሃት ከተደበቀንበት እንውጣና ሕይወትን እንኑራት!
ወሳኝ ጥያቄዎች፡-
1. አሁን የምኖረው ኑሮ ያለኝን እምቅ ብቃት በሙሉ ተጠቅሜ ነው ወይስ ገና መድረስ የምችልበት ደረጃ አለ?
2. ካለሁበት ደረጃ ወደተሻለው አልፎ ለመሄድ ማድረግ የምችለው ነገር ምንድን ነው?
3. ያንን እንዳላደርግ የያዘኝ ነገር ምንድን ነው?
4. ይህንን ሁኔታ በምን መልኩ ልቅረፈው?
5. ይህንን የለውጥ ጉዞ ለመጀመር ምን ላድረግ? ማንን ላነጋገር? ከመቼ ልጀምር?
Dr. Eyob Mamo