ፕሬዝደንቱ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና፣ በተለያዩ ዘመናትና ስልጣኔዎች የተለያዩ የአመራር ፍልስፍናዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በአሁኑ “ድህረ-እውነት” አለም ውስጥ፣ ሁሉም እውነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ በመግባቱ፣ አመራር ከምንጊዜውም በላይ ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ገልጸዋል።
“እኛ ሰዎች ራሳችንን ለመሪነት ብቁ ማድረግ ካልቻልን፣ እኛው የፈጠርነው አልጎሪዝም ይመራናል” ሲሉ ተናግረው፣ “ነባር ነገሮች ሁሉ ፈርሰው አዳዲስ ነገሮች በፍጥነት እየተጀመሩ ባለበት በዚህ አለም፣ ረጋ ብሎ የወደፊቱን ጊዜ ለመወሰን የሚቻለው በመሪነት ብቻ ነው” ብለዋል።
ለዘመናችን የሚያስፈልገው መሪ ደፋር ብቻ ሳይሆን፣ ድፍረትንና ወኔን ከጥበብ ጋር የሚያስተሳስር አመራር መሆኑን ፕሬዝደንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ባለአደራ መሪ” የምንለው አመራር የተሰበረን የሚጠግን፣ መቀጠል ያለበትን የሚያስቀጥል፣ አላስፈላጊውን ቆርጦ የሚጥል፣ ነገን የሚተነብይ፣ አዲሱን ነገር ተቀብሎና አጎልብቶ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ዛዲግ በአሁኑ ወቅት ያሉ ወጣቶች የሚቆጣጠራቸውን ሳይሆን የሚያሳትፋቸውን ስርዓት እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፣ መሪዎች ስርዓትን መሰረት አድርጎ ከመስራት ባሻገር ከስርዓት ውጪም ማሰብ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ከቴክኒካዊ አመራር ይልቅ፣ ራሱን ከጊዜና ሁኔታዎች ጋር የሚያላምድ እና ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት አቅም ያለው አመራር እንደሚያስፈልግም አቶ ዛዲግ ገልጸዋል።
ስልጠናው በቀጣይ ቀናት ውሎው በአቶ ዛዲግ ከሚሰጠው ማብራርያ በተጨማሪ አሳታፊ ውይይቶች እንደሚኖሩት ተገልጿል።











