እውን ሙዚቃና ዘፈን በኢስላም አልተከለከለምን? ✍🏻 ሙሀመድ ሀሰን ማሜ (ጥር 2003) ┄┄┉┉✽»🌼»✽┉┉┄┄ አንደሚታወቀው ኢስላም ሰፊና ጥልቅ አስተምህሮቶች፤ ረቂቅና ጥልቅ መመሪያዎችና ድንጋጌዎች አሉት፡፡ ሁሉንም የህይወት ዘርፎች ዳሷል። ሳያስተምረን ያለፈው የህይወት ጉዳይ የለም። በተለያየ መልክና ዘዴ እያንዳንዱን የህይወት ክፍል በመዳሰስም ወደር የሌለው ሃይማኖት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህንንም እውነታ የማንኛውም አማኝ ልቦናና ህሊና ያውቀዋል፡፡ ሆኖም በኢስላም ድንጋጌ እና መመሪያ ላይ በየጊዜው እና በየወቅቱ የተለያዩ ብዥታዎችና ውዥንብሮችን የሚፈጥሩ ሰዎች አልጠፉም፣ ነበሩም፣ አሉም፣ ይኖራሉም፡፡ በየጊዜው ብቅ ጥልቅ ከሚሉ በርካታ ውዥንብሮች መካከል የሙዚቃን ብይን የተመለከተው ይጠቀሳል። የራሳቸውን ግንዛቤ ለማስተላለፍ ሲፈልጉ፤ ኢስላም ስለዘፈንም ይሁን ስለሙዚቃ ክልክልነት የተናገረው ነገር የለም፡፡ ክልክል ለመሆኑ የቀረቡ መረጃዎችንም የወደቁና ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆኑ፤ ሲጠኑ በሁለት እግር መቆም የማይችሉ እንደሆኑ አድርገው በማቅረብ የሚነዙት ብዥታ ተራ አሉባልታ እንደሆነ በእዚህ መልዕክቴ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ በተለይም ሰሞኑን አቶ ሀሰን ታጁ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ የጣዕም ልኬት የሙዚቃ ዝግጅት ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ይህ አይነቱን አመለካከት በስፋት ስላብራራ አጠር ያለ ምላሽ አዘጋጅቻለው። አላህ ስራችንን ሁሉ በኢኽላስ የተፈፀመ እንዲያደርገውነ እለምነዋለሁ። እግዛንም ከእርሱ ብቻ እጠይቃለሁ፡፡ ዘፈንና ሙዚቃ በኢስላም የተከለከለ መሆኑን በተለያዩ ኢስላማዊ መረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ 1ኛ- ከቁርአን 2ኛ- ከሐዲስ 3ኛ- ከሰሃቦች 4ኛ- ከታቢዒዮች 5ኛ- ከአራቱ መዝሃቦች 6ኛ - ከኢጅማዑ አሰለፍ 1ኛ- ከቁርአን በሱረቱል ሉቅማን ቁጥር 6 وَمِنَ النَّاسِ مَن يَشْتَرِي لَهْوَ الْحَدِيثِ لِيُضِلَّ عَن سَبِيلِ اللَّهِ بِغَيْرِ عِلْمٍ وَيَتَّخِذَهَا هُزُوًا ۚ أُولَٰئِكَ لَهُمْ عَذَابٌ مُّهِينٌ [٣١:٦] “ከሰዎች ያለ እውቀት ሆኖ ከአላህ መንገድ ሊያሳስትና ማላገጫ አድርጎ ሊይዛት አታላይ ወሬን (ለህወል ሀዲስ) የሚገዛ አለ፤ እነዚያ እነሱ አዋራጅ ቅጣት አላቸው፡፡” በእዚህ አንቀፅ ውስጥ “ለህወል ሀዲስ” (አታላይ ወሬ) ተብሎ የተሰየመውና ቅጣቱም አወራጅ ተብሎ የተዛተበት ምን ይሆን? መልሱን ከሰሃቦች ማግኘት ይቻላል፡፡ ሀ. አብድላህ አብኑ መስዑድ (ስለቁርአን ጥልቅ እውቀት ባላቸው ስመጥር ሰሃባ አንዱ ነው፡፡) ስለ “ለህወል ሀዲስ” (አታላይ ወሬ) ሲጠየቅ ሶስት ጊዜ በመማል “ዘፈን ነው ዘፈን ነው ዘፈን ነው” በማለት መመለሱን ኢብኑ አቡ ሸይባ፣ ኢብኑ ጀሪር፣ አልሃኪም፣ አልበይሀቂ እና ኢብልጀውዚ ዘግበውታል፡፡ ለ. አብደላህ ኢብኑ ዐባስ (የዑማው አዋቂና በቁርአን ማብራሪያ ላቅ ያለ እውቀት ያለውና ረሱልም “አላህ ሆይ ሃይማኖቱን አስገንዝበው የቁርአንንም ማብራሪያ አሳውቀው፡፡” ብለው ዱዓእ ያደረጉለት ስመ ጥር ሰሃባ ነው፡፡) ስለ (ለህወል ሀዲስ) “ዘፈንና መሰሎቹ ናቸው” ማለቱን ኢብኑ አቡ ሸይባ፣ (ቡኻሪ፣ ኢብኑ ጀሪር፣ አልበይሀቂ፣ እና ኢብኑ ጀውዚ ዘግበውታል፡፡) ሐ. አብደላህ ኢብኑ ዑመር (የመዲና ሙፍቲና የፊቂህ ምሁር ) ለሕወል ሀዲስን በማስመልከት “እርሱም ዘፈን ነው” በማለት አብራርቶታል፡፡ መ. ጃቢር ኢብኑ አብደላህ (ከኢብኑ ዑመር ቀጥሎ የመዲና ሰዎች ፊቂህ እንዲሁም ሙፍቲ የነበረው) “ዘፈንና ማድመጡ ነው” ማለቱን ኢብኑ ጀሪር ዘግበዋል፡፡ ታዲያ ከእነዚህ ታላላቅና ስመጥር ሰሃቦች ይህን አንቀፅ በተመለከተ (ዘፈን) መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ የሰሃቦች ማብራሪያ ማስረጃ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህንም ማብራሪያ የተቃረነ አንድም ሰሃባ የለም፡፡ ሰሃቦችም እንዲህ ብለው እንደተረጐሙት ሁሉ ታቢዒዮችም በተመሳሳይ መልኩ አብራርተውታል፡፡ እንደሚከተለውም ዝርዝራቸውን እጠቅሳለሁ፡፡ 1.ሙጃሂድ ኢብኑ ጃቢር 2. ዒክሪማህ 3. መክሁል 4.ኢብራሂም አል ነኸዒ 5. ዐጣእ 6.ሰዒድ ኢብኑ ጁበይ 7.አል ሐሰን አል በስሪ 8.ቀታዳህ ኢብኑ ደዓማ 9.መይሙን ኢብኑ ሚህራን 1ዐ. ሀቢብ ኢብኑ አቢሳቢት 11. ዐምር ኢብኑ ሹዓይብ 12. አብዱልመሊክ ኢብኑ ጁረይጅ 13. ሰኢድ ኢብኑልሙሰይብ ናቸዉ፡፡ ሱረቱ ነጅም ቁጥር 59 – 61 أَفَمِنْ هَٰذَا الْحَدِيثِ تَعْجَبُونَ [٥٣:٥٩]وَتَضْحَكُونَ وَلَا تَبْكُونَ [٥٣:٦٠]وَأَنتُمْ سَامِدُونَ [٥٣:٦١] “በዚህ ንግግር ትደነቃላችሁን?! ትስቃላችሁምን? አታለቅሱምን? እናንተም ዘንጊዎች ናችሁ፡፡” ይህንም አንቀፅ በማስመልከት ዘንጊዎች ተብሎ የተተረጐመው ቃል በአረብኛው “ሳሚዱን” የሚለው ቃል ሲሆን ትርጉሙን በተመለከተ የየመን ቋንቋ እንደሆ በመጥቀስ “ዘፈን” እንደሆነ አብደላህ ኢብኑ ዐባስ ፣ ሙጃሂድ፣ ዒክሪማና አደሃክ ተናግረዋል፡፡ ሱረቱል ኢስራእ ቁጥር 64 وَاسْتَفْزِزْ مَنِ اسْتَطَعْتَ مِنْهُم بِصَوْتِكَ وَأَجْلِبْ عَلَيْهِم بِخَيْلِكَ وَرَجِلِكَ وَشَارِكْهُمْ فِي الْأَمْوَالِ وَالْأَوْلَادِ “ከእነሱ ያቻልከውንም ሰው በድምፅህ አታል በእነሱም ላይ በፈረሶኞችህም ለልብ በገንዘቦቻቸውም፣ በልጆቻቸውም ተጋራቸው፡፡” ሙጃሂድ ኢብኑ ጃብር (የአብደላህ ኢብኑ ዓባስ ታላቅ ተማሪ) የኢብሊስ ድምፅ ምንነት ሲገልፁ እንዲህ ነበር ያሉት፡፡ “እርሱም ጊና (ዘፈን)፣ ሙዚቃ መሳሪያ፣ ላግጣና ከንቱ ነገር ነው፡፡” አድሃክም የዘፋኝ (የሙዚቃ መሳሪያ) ድምፅ ነው” ብለዋል ኢብኑል ቀይምም እንዲህ በማለት ስለዘፈን ሁኔታ ይገልፃሉ :- “ዘፈን ከታላላቅ የሰይጣን ድምፃችና ነፍስን የሚያስበረግግበት፣ የሚረብሽበት እና ሰላም የሚነሰት ለመሆኑ አያጠራጥርም የቁርአን ወደሚረጋጋበት፣ ሰላም የሚያገኝበትና ወደጌታዋ እንድትመለስ የሚያደርገውን ተቃራኒ ነው፡፡” 👉 ቀሪውን ክፍል በሚከተለው ሊንክ ያንብቡ https://nesiha.com/%e1%8a%a5%e1%8b%8d%e1%8a%95-%e1%88%99%e1%8b%9a%e1%89%83%e1%8a%93-%e1%8b%98%e1%8d%88%e1%8a%95-%e1%89%a0%e1%8a%a2%e1%88%b5%e1%88%8b%e1%88%9d-%e1%8a%a0%e1%88%8d%e1%89%b0%e1%8a%a8%e1%88%88%e1%8a%a8/ ┄┄┉┉✽»🌼»✽┉┉┄┄ © ተንቢሀት @tenbihat
1