በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ሱሉላ ፍንጫኣ ወረዳ በሚገኘው የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የ4 ሚሊሻዎችን እና የአንድ ሰላማዊ ነዋሪ ህይወት ማለፉን ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዘግቧል።
ሁለት የፋብሪካው ሰራተኞችም ታግተው ተወስደዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ተሰብሮ ገንዘብ መዘረፉን እንዲሁም ወደ 40 የሚጠጉ ሞተር ሳይክሎችና አራት መኪኖች መቃጠላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከ2015 ዓ/ም ወዲህ ከፍተኛ ነው የተባለው የታጣቂዎቹ ጥቃት የተፈጸመው ትላንት ማለዳ 11 ሰዓት ገደማ ነው።
ታጣቂዎቹ ወደ ፋብሪካው ግቢ በመግባት ጥቃቱን ያደሱ ሲሆን፣ የጸጥታ አካላት አጸፋዊ እርምጃ በመውሰዳቸው ታጣቂዎቹ ከፋብሪካው ወጣ ብለው ሲሸሹ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ድብደባ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። ሆኖም በታጣቂዎቹ ላይ ስለደረሰው ጉዳት የደረሰ የተረጋገጠ መረጃ የለም።
ከፋብሪካው እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለማግኘት ጥረት ያደረገው ሬድዮ ጣቢያው ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።
ፋብሪካው በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም በደረሰበት ተመሳሳይ ጥቃት በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራ እንደደረሰበት መዘገቡ ይታወሳል።
ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ/ም

October 21, 2026 564