ክብር በማማ
የዐፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ በተለያየ የጦር አካዳሚ የሚጠና ሲሆን፤ “የዓለማችን አጭሩ የክተት ዓዋጅ” ተብሎ ይጠራል። አብዛኛው የጦር አዋጅ ከሃያ ገጽ እስከ መቶ ገጽ እንደ ሚፈጅ ልብ ይሏል። የምኒልክ ወርቃማው የክተት ዐዋጅ አንድ ገጽ ባትሞላም፥ ብዙ የሚፈከርበትና በብዙ እንደምታ የሚታይ ሲኾን ከዋናው ነጥብ ላለመራቅ፥ መለኮት-ተኮር (theocentric) እና ሰው ተኮር (anthropocentric) ጎኖች አሉት ብሎ ጥቁምታ ሰጥቶ ማለፉ ይበጃል። “አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም” … በሚልና … “ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ!” በሚል ይቀነበባል። ይመር የተሰኘው ገጸሰብ ይሄን ዐዋጅ የሰማው “ታይሞስ” በተሰኘው ዕውቅና እና ክብር ፈላጊው በኾነው የነፍስ ክፍል ውስጥ ባለው ጆሮ በኩል ነበር።
ክብረ-ነክ የሆኑ ጥቃቶች ለሀገራት የኃይል ምንጮች እንደሆኑ ፍራንሲስ ፉኩያማ ‹Identity› በተሰኘ መጽሐፉ ያትታል። በኛ ሀገር ግን ከኃይል ምንጭነትም ይሻገራል። የእናት ሀገር ክብር ሲነካ ሕዝቡ ያብራል። አንድያ ነፍሱን ይገብራል። ይመር የተሰኘው አዝማሪው ገጸባሕርይ ግን አሪስቶክራት ኅብረተሰብ ዘንድ እንዳሉት ሜጋሎቲሚያ (ከሌሎች እንደሚልቁ እውቅናን የሚሹ)፤ ክብርን ፈልጎ ነበር ሊዘምት የወጠነው። የአርስቶትል ሪፐብሊክ ላይ እንደተጠቀሰው፥ “ታይሞስ” በተሰኘው የዕውቅናን ክብር የሚፈልገው የነፍስ ክፍል ገፍቶት ነው፣ ከሞት አፍንጫ ሥር ለመርመስመስ ልቡ የተነሳሳው። ለዚህ ነው ሰዒድ የተሰኘው ወዳጁ፤ “ጃኖይ ዐይን እንዲትገባ ቀዴም ቀዴም ማለት አለብህ” ያለው ትዝ የሚለው። ለዚያ ነው “ አቤቱ ፈጣሪየ … የልቤን ቁስል ምታቅ አንተ ብቻ ነህ። ተወረይሉ ወጥቸ … ተሰው ተቆጥሬ … ተከብሬ … ምመኘው እሱን ብቻ ነው” እያለ ከራሱ ጋር የሚነጋገረው። የኋላ ኋላ ግን ከወረኢሉ ተነስተው፥ የደሴን እንቆቅልሽ ፈትተው፥ የአላማጣን መንታ አልፈው፥ የመቀሌን የስሜት ገበታን ተወጥተው፥ ይሐ ላይ አኮብኩበው፥ የዐድዋ የገድል አክሊል ዘንድ ሲደርሱ የወረኢሉው ይመር በዐድዋው ይመር ይተካል። የይመር “ታይሞስ” ይሟሽሻል። አሰቃቂውን ጦርነት ከተካፈለ በኋላ፣ “ያንን ሰፊ የጦር አውድማ፣ ያንን ገላጣ መሬት የከበቡትን ተራሮች አንድ በአንድ አየና ግዝፈታቸው አስፈራው፣ ግርማ ሞገሳቸው አክብሮት፣ አድናቆትና ፍርሐት ጫሩበት። በነሱ ፊት ከሰናፍጭ ያነሰ መሆኑ ታወቀው። “ተይመር ወዲያ” የሚለው ፈሊጡ ብልጭ አለለት፤ ልኩን አለማወቁን ጠቆመው። ”ተራሮቹ“ በእናት ሀገርህ ክብር ውስጥ ነው የአንተም ክብር ያለው!” ሲሉ ሰበኩት። ጃንሆይ ፊት ቀርቦ መሞገስ፣ መወደስ ውጥኑ የነበረው ይመር እያለ ሚስቱ ዘውዴ ምርኮዋን ይዛ ስታልፍ ንጉሠ ነገሥቱ እጅ ነሷት። ወለፈንዴ ብሎ ዝም! ይመር የዴቪድ ሊቨንግስተን ወንድም የጣለውን ካርታም አይደል ያነሳው? ታዋቂ መኾን የሚፈልገው የዴቪድ ሊቪንግስተን ወንድም የሚታወቀው፥
የዴቪድ ሊቨንግስተን ወንድም በሚል ቀጭንዬ መስመርም አይደል?ተጨማሪ ያንብቡ
https://t.ly/JyOt7











