እጠብቃታለሁ...ደግሞም ትመጣለች (ክፍል ሁለት) ዛሬ በናፍቆም ብዛት እያሰብኳት የምጠብቀታ እንስት ያን ቀን ነበር ቤቴ ገብታ ሽር ጉዷን የጀመረችው። ላያት ሰው የሰነበተች እመቤት እንጂ ከደቂቃዎች በፊት ከቤቱ የገባች እንግዳ አትመስልም። ቡና እያፈላችልኝ በስረዓቱ ተዋወቅን። "በኩራት" አለችኝ ስሟን። ስሟም መልኳም ሁሉነገሯ የሚያምር ቆንጆ። የራሷን ታሪክ ከተረከችልኝ በኋላ ስለእኔ መጠየቅ ገባች። "ለምንድን ነው ብቻህን የምትኖረው? "ብቻዬን አይደለሁም፤ ፈጣሪ ከእኔ ጋር ነው።" በስሱ ሳቀችና "እሺ ለምን አላገባህም?" አለችኝ "እንዳንቺ አይነት ቆንጆ ካልሆነ አላገባም ብዬ በመድረቄ።" እንደመሽኮርመም ብላ "ብቻ መኖር አያስጠላም ግን?" "ከአሁን በኋላ ሊያስጠላኝ ነው።" "እንዴት?" "አንቺን ካየሁሽ በኋላ ብቻዬን መኖሬ እያስጠላኝ ነው።" አልኳት ሳቅ ብዬ። አሁንም ተሽኮረመመች። ደስ አለችኝ፤ ማሽኮርመም ግን ደስ ይላላ? "ብዙ ጊዜ እዚሁ ሰፈር ነው የማይህ፤ ስራ የለህም እንዴ?" አለች "ከቤቴ ሁኜ ነው የምሰራ ለዛ ነው። ግን ብዙ ጊዜ አይሃለሁ ስትዪ..." "ኧረ እኔ ሁሌ ነው የማይህ....ስትወጣና ስትገባ እየጠበኩ....ሱቅ ሳልኖር በዛ ካለፍክ እህቴ ትጠራኛለች እየሮጥኩ መጥቼ አይሃለሁ። ከቤት ያልወጣህ ቀን አቤት የቀኑ ርዝመት፤ ሲያስጠላ።" አለች እነኚያን የሚያማምሩ አይኖቿን እኔ ላይ እንደተከለች። አይኗ ፍቅሯን ይናገራል፤ ፊቷ ለረጅም ጊዜ የፈለገችውን በማግኘት የረካች ነፍስ መሆኗን ይመሰክራል። "አንተስ አይተኸኝ አታውቅም?" የሚለው ጥያቄ በሃሳብ ከሄድኩበት መለሰኝ። እርሷም መልሴን በጉጉት እንደሚጠብቅ ሰው አይኔ አይኔ ማየት ጀመረች። "የሆነ ቀን ሱቅ ውስጥ ያየሁሽ መሰለኝ" አልኳት። ያኮረፈ ፊት እያሳየችን "መሰለኝ? በቃ?" ብላ አቀርቅራ ማርገብገቧን ቀጠለች። "በጣም ቆንጆ ነሽ።" አልኳት ከገባችበት ድባቴ ለመመለስ፤ በእርግጥ በጣም ቆንጆ ናት። "የእውነት ቆንጆ ነኝ?" አለች በድባቴ የጠቆረው ፊቷ ለፍካት ቦታ እየለቀቀ። በቃ በኩራት እንዲህ ነች ኩርፊያም ንዴትም ማይሰነብቱላት። "በጣም እንጂ! ሰው ነግሮሽ አያውቅም?" "ለአንተ ቆንጆ ከሆንኩ ይበቃኛል።" ብላ ቀጠለች። "ለምን እንደመጣሁ ግን ታውቃለህ?" "አላውቅም።" "አትታዘበኝም ልንገርህ?" "እንደውም ደስ ነው የሚለኝ።" "Promise?" "Promise!" ቃሌን ሰጠኋት። "ቅድም ብና ስትገዛ ብና የምታፈላ ሴት የመጣች መስሎኝ ለመረበሽ ነበር የመጣሁት። ልክ ቡና ገዝተህ ስትመለስ ምን እንደነካኝ አላውቅም፤ አቁነጠነጠኝ። መርሳት አልቻልኩም። ምመጣበት ምክንያት ስፈልግ ስኳር ይዞ መምጣት ታየኝ።" አለች እንደ ማፈር ብላ። ግልጸኝነቷን ወደድኩት፤ በመጀመሪያ ቀን እንደቀልድ ከቤቴ ገብታ ወዳጅነት መፍጠሯ የጤና አልመስል ቢለኝም ልቤ ግን ለእርሷ ደጁን መዝጋት ተሰኖት በቀላሉ እጁን ሲሰጥ ተሰማኝ። ከዛን ቀን በኋላ ዘወትር ከሰዓት አስር ሰዓት ሲል የውጪው በር ይንኳኳል። "ድም ድም ድም......" የማይቋረጥ መንኳኳት። በሩን እከፍትላታለሁ ተጠምጥማ ሰላም ትለኝና ቀድማኝ ወደ ቤቴ ትገባለች። ወዲያው በብቸንነት በጸጥታ የዋለውን ቤት በሰላምና በፍቅር ሞቅ ታደርገዋለች። አስቀድማ የምትገባው ወደ መኝታ ክፍሌ ነው፤ የማዝረከርካቸውን ልብሶች ለማስተካከል። (ሃሳባችሁን አልሳትኩትም፤ ተበላሽታችኋል።) የተዝረከረኩ ልብሶቼን ስትመለከት "ሌላው አብርሽ" እያለች በፍጥነት ማስተካከል ትጀምራለች (አብርሽ ታናሽ ወንድሟ ነው)፤ "ቤት በማዝረክረክ አንተና እርሱ የተለየ ክህሎት አላችሁ እኮ። ትናንት አይደል ያስተካከልኩት?" ስታጉረመርም ከእኔ መልስ አትጠብቅም። እኔም ምንም አልላትም። እንዲህ ስታጉረመርም ደስ ስለምትለኝ ፈገግ ብዬ አያታለሁ። ከተለያየን ወራት ቢቆጠርም ያሞቀችው ቤቴ በእርሷ መጥፋት ቢቀዛቀዝም እነዚህ ሁሉ ትዝታዎቼ ለአፍታም ሊረሱኝ አልቻሉም። ዛሬም ላይ ሁኜ እነኛን ጊዜያት እያሰብኩ በናፍቆት እጠብቃታለሁ። ከዛሬ ነገ መጣች እያልኩ የደጅ ደጁን እያየሁ እጠብቃታለሁ። ይቀጥላል...
እጠብቃታለሁ...ደግሞም ትመጣለች (ክፍል ሁለት) ዛሬ በናፍቆም ብዛት እያሰብኳት የምጠብቀታ እንስት ያን ቀን… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME
August 9, 2025 463 3