ምትሰሙትን ብቻ ሳይሆን ምታዩትን ሁሉ አትመኑ.... ከድርጊቶች በላይ ድርጊቶቹ የተደረጉበት መንስዔ ምክንያት… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

ምትሰሙትን ብቻ ሳይሆን ምታዩትን ሁሉ አትመኑ.... ከድርጊቶች በላይ ድርጊቶቹ የተደረጉበት መንስዔ ምክንያት ነው ዋናው ቁም ነገሩ። ከብዙ እኩይ ድርጊቶች ጀርባ መልካም፤ ከብዙ በጎ ድርጊቶች ጀርባ አልባሌ ገፊ ምክንያቶች ሊኖሩ የመቻላቸው ሃቅ ሊረሳ አይገባምና። "ሰው አልፈልግም፤ ብቻዬን መኖር እችላለሁ!" ማለት የጥንካሬ መገለጫ ተደርጎ ቢወሰድም ቅሉ ምንጩ ከሰው ጋር መኖር መፍራት የሚሆንበት ጊዜ የትየለሌ ነው። ያለመፈለግና ያለመወደድ ፍረሃት ሲያይል እውነትን በራስ ልክ ለመስፋትና ራስን ለማሳመን የሚደረግ ሽሽት "ሰው አልፈልግም፤ ብቻዬን እኖራለሁ።" የሚል ጩኸት ይወልዳል። በዚህ በተሳሳተ ሂሳብ ብዙ ፍርሃቶች ጥንካሬ፤ ብዙ ፈሪዎች ጠንካራ ተደርገው ተቆጥረዋል። አንዳንድ ኩርፊያዎችም ቅይማት የወለዳቸው ቢመስሉም ጠልቃችሁ ብትመለከቷቸው ግን ጉዳዩ ሌላ ነው።  አንዳንዴ ኩርፊያ ትኩረትና እንክብካቤ ለማግኘት የሚደረግ ትግል ሁኖ እናገኘዋለን። አንዳንድ የፍቅር ተግባራት ማለትም እንክብካቤ፣ ፍቅር መስጠት፣ ዋጋ መክፈል እውነተኛ ከሆነ አፍቃሪ ልብ ብቻ ይገኛሉ ብሎ ማመን ዘበት ነው። አልፎ አልፎ "በምሰጠው ፋንታ ላገኝ እችላለሁ፤ በሰጠሁት ልክ እወደድ ይሆናል።" በሚል በሰጥቶ መቀበል ስሌት የተሰላ ሁኖ ይገኛል። የተንከባከባችሁ፣ ትኩረት የሰጣችሁ ብዙ ርቀት የተጓዘላልችሁ ሁሉ አፍቅሯችሁ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ትጋቶች ትጉ ከሆኑ ስብዕና የተወለዱ አይደሉም። መደነቅንና የትኩረት ማዕከል ለመሆን ትጉ መስሎ መቅረብ አዋጭ መስሎ የታያቸው ጮሌዎች ቀመር ሊሆን ይችላል። ልግስና ሁሉ በቀናነት እንደማይደረገ ማስተዋል ተገቢ ነው። አንዳንድ ልግስናዎች በከበባቸው ሰው መካከል የደግነት ካባን ለመደረብ በሚፍጨረጨሩ የሚተወን ድራማ ነው። ክርሰቶስ በምድር በተመላለሰበት ዘመን እንደ ፈሪሳውያን ወግ አጥባቂና በሐይማኖት አክራሪ ተደርጎ የሚቆጠር አልነበረም። ኢየሱስ ግን የእፉኝት ልጆችና ግብዞች እያለ ነበር የሚጠራቸው። ምክንያቱም የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያደርጉበት መንስዔ ያ ክፉ ልብ ነውና። ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚናገሩትን ከማመን የሚያደርጉት መመልከት ይባላል። በከፊል እውነት ነው። እኔ ግን እላችኋለሁ የምትሰሙትን ብቻ ሳይሆን የምታዩትን ጠይቁ። ድርጊቶችን ብቻ ሳይሆን ድርጊቶች የተደረጉበትም ምክንያት አስተውላችሁ ለመመልከት ሞክሩ። https://t.me/Yeroreflect

July 28, 2025 303 1