ያለቀውን ጦርነት ሲዋጋ የኖረው ወታደር... ሂሮ ኦናዳ (Hiroo onada) ይባላል፤ በሁለተኛው የአለም… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

ያለቀውን ጦርነት ሲዋጋ የኖረው ወታደር... ሂሮ ኦናዳ (Hiroo onada) ይባላል፤ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ጦር አባል ሁኖ በፊሊፒንስ አንድ ደሴት ላይ ዘመተ። ታዲያ በዚህ ዘመቻ ላይ እንዳሉ የአሜሪካ የጦር አይሮፕላኖች የጃፓን የጦር ይዞታዎች በመደብደብ የጃፓንን ጦር ያንኮታኩቱታል። ይህን ተከትሎ የኦናዳ አዛዥ የቀሩትን የጃፓን ወታደሮች እጅ እንዳይሰጡና የጃፓን ጦር መልሶ ይዞታውን እስክይዝ በጽናት እንዲታገሉ ትዕዛዝ ይሰጣል። ነገሩ እንደታሰበው ሳይሆን ይቀርና የሂሮ ኦናዳ አዛዥ ጨምሮ ብዙ ወታደሮች እጃቸውን ይሰጣሉ። ኦናዳ ግን የዚህ ሁሉ መረጃ አልነበረውም፤ ውጊያው እየበረታ ሲሄድ በቅርበት ወደ በነበረ ጫቃ መሽጎ የጎሪላ ውጊያ ማድረግ ይመርጣል። ከጊዜያት በኋላ ጦርነቱ መጠናቀቁን፤ ጃፓንም ጦረነቱን እንደተሸነፈች የሚያሳውቁ በራሪ ወረቀቶች በሰማይ ከሚበረው አውሮፕላን መዝነብ ጀመሩ ኦናዳ ግን ከጠላት አውሮፕላን የሚወርደውን ዜና ለማመን አልፈለገም። የጠላት ፕሮፖጋንዳ መስሎት ነበረና። እና በዚያ ጫቃ ነፍጡን እንዳነገበ ለ30 ዓመት ከረመ። አንዳንዴ ከጫቃ እየወጠ (ከእርሱ ጋር ከነበሩ ጥቂት ወታደሮች፤ በጊዜ ሂደት አንድ በአንድ አልቀው ብቻውን እስኪቀር ማለት ነው) በአቅራቢያው በሚገኙ መንደሮች ላይ ጥቃት ይከፍታል። ምክንያቱም በዚያ መንደር የሚኖሩ ፊሊፒናዊያን የአሜሪካ መረጃ አቃባይ እንደሆነ ያስብ ስለነበረ ነው (ከ30 ዓመት በፊት በነበረ እሳቤ)። ኦናዳ በተለያዩ ጊዜያት እጁን እንዲሰጥ ጥረት የተደረገ ቢሆንም አሻፈረኝ በማለቱ በመጨረሻም ከጃፓን መንግስት ጣልቃ ገብነት በቀድሞ የጦር አዛዡ ትዕዛዝ እጁን ሰጥቶ ወደ ሃገሩ ጃፓን ተመለሰ። ምስኪኑ ኦናዳ 30 ዓመታት በሌለ ጦርነት ተዋግቷል፤ ሶስት አስርት ዓመታትን በጫካ መሽጓል፤ የደፈጣ ውጊያ ከፍቷል፤ እርባና ቢስ በሆኑ ግጭቶች ህይወታቸው ያሳጣቸውና ያቆሰላቸው በርካቶች ናቸው። ባለቀ በተጠናቀቀና በተረሳ ጦርነት። ዓለም በቋጨው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ተወሽቆ እድሜውን ቀርጥፎ የበላ ምስኪን ወታደር፤ ኦናዳ። የምስኪኑን ኦናዳ ሕይወት በየፊናቸው የሚኖሩ ጥቂት አይደሉም። በሌለ ጦርነት ሲዋጉ፣ ባከተመ ውጊያ ሲዘምቱ፣ እድሜቸውን ለሌለ ጠላት ሲሰው የሚኖሩ በርካታ ናቸው። ባለፉት ዘመናት ጠባሳዎች የዛሬን ሰላማዊ አየር መተንፈስ ተስኗቸው፤ ትናንት በገጠማቸው አሉታዊ የሕይወት ገጽታ ከዛሬ እንደተቃረኑ የሚኖሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው። አንዳንዶቻችን በሕይወት ውስጥ ወደፊት መራመድ የከበደን የሌለውን ጠላት ወይም አደጋ ፈርተን ነው፤ አዲስ የሕይወት መንገድ ላይ ላለመራመድ ፈራተባ የምንለው በምናባችን ያበጀነው "ደመኛ" አሊያም ከትናትን የሕይወት ምዕራፍ ተውሰን ትግል የገጠምነው የውሰት ጠላት ነው። ብዙዎቻችን ያልተኛነው ታችምና ያየነው ሕልም አይሉት ቅዠት እንዳይደገም በሚል ፍርሃት ነው። አዎን ብዙዎች በሌለ ጦርነትና ለሌለ ጠላት ምሽግ መሽገን የፍርሃት ሕይወት እንመራለን። እስቲ አንዴ ከተደበቅንባቸው የፍረሃት ጢሻዎች ውስጥ ወጥተን ዙሪያችንን እንቃኝ። በመንገድ አንዳች ነገር ይገጥመን ይሆን በሚል ፍረሃት ተተብትበን ከተቀመጥንበት ምሽጋችን እንውጣ። ወደፊት እንመልከት፤ እንጓዝ። ልክ እንደ ልጅነታችን "አያ ጅቦ ውጪ አለ" በሚል ማስፈራሪያ ተዘግተን ከተቀመጥንበት ጉያችን፣ በስጋት ከተጠለልንበት ታዛችን እንውጣ። ነገን በተስፋ ተመልክተን ደፍረን ወደፊት እንጓዝ። https://t.me/Yeroreflect

July 23, 2025 302 2