እንደ ቀልድ የጣሉት.... እንደ ቀልድ ነበር፤ በአስቸኳይ ካላገኘውህ ብላ አጣድፋኝ ያገኘችኝ። የቀጠረችኝ… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

እንደ ቀልድ የጣሉት.... እንደ ቀልድ ነበር፤ በአስቸኳይ ካላገኘውህ ብላ አጣድፋኝ ያገኘችኝ። የቀጠረችኝ ዘወትር ከምናዘወትርባቸው ካፌዎች ከአንዱ አልነበረም፤ በሰው ስለሚጨናነቅ ከማልመርጠው ካፌ ስትቀጥረኝ መጀመሪያውኑ ገርሞኝ ነበር። ድሮ ድሮ ጓደኞቿ ራሱ እዛ ሊያገኟት ሲፈልጉ "ውይ እኔ እዛ አልመጣም፤ ውዴ አይወደውም" ትል ነበረ። ታዲያ ከዚያች ከማልወዳት ካፌ ተሰይሜ እንደ ቀላል ነገር ምንም እንዳልሆነ በሚመስል ድመጸት "በቃን እናቁም" አለችኝ። የምሰማውን አላመንኩም፤ በሰው በተጣበበ ካፌ ከጫጫታው መሃል የሌላ ሰው ንግግር የሰማው መስሎኝ ግራ ቀኝ አማትሬ ነበር። ግን ራሷ ነች፤ ከተቀመጠችበት ወንበር ላይ ከጀርባዋ ተደግፋ፤ ዘና ብላ "ይብቃን"። ከፊቷ የቀረበላትን ማኪያቶ የማማሰል ያህል ሳይከብዳት "እንለያይ" አለች። ዛሬ እንደ ዘበት ለማፍረስ የቀለላትን ግንኙነት የክፍለ ዘመናት ዕድሜ ቢቸራት መልሳ መገንባት ላትችል እንደምትችል ገብቷት ይሆን? ይሄ ውሳኔዋ ከዚህ ካፌ ከወጣን በኋላ ተመልሶ ላይካብ ተንዶ እንደሚቀር እርካብ መሆኑን አውቋው ይሆን? አይመስለኝም። የተወሰነ ፊቷን አተኩሬ ተመለከትኩና። "ስለ ምንድን ነው የምታወሪው?" አልኳት "ስለ እኔና ስለ አንተ ግንኙነት፤ ይሄ ሪሌሺንሺፕ እዚህ ጋር መቆም አለበት።" አለች በልበ ሙሉነት። ፈገግ አስባለኝ። አልተበሳጨኹም! ይሄ ግንኙነት ቢፈርስ የምጎዳው ነገር አለ? በፍጹም፤ አይመስለኝም። ከዕለታት በአንዱ ቀን ተነስታ ካልሄድኩ የምትል ሴት በመሄዷ ምን ይቀርብኛል። መንገደኛ ልብ አስጠልዬ የምኖርበት ምንም ዕዳ ኑሮብኝ? ግና ክፉም ደግም ከመናገሬ በፊት፤ ፊቷን እያጤንኩት የተወሰኑ ጥያቄዎችን ወረወርኩላት "እየቀለድሽ ወይንም Prank ለማድግ ምናምን አስበሽ አይደለማ።" ጠየኳት "ምጃጃልበት ጊዜ የለኝም" አጠር ቆምጠጥ ያለ መልስ። አንገቴን ታች ላይ ነቀነቁት፤ ይመስለኛል "ጥጋብሽ እዚህ ደርሷል?" እያልኩ ነው። "እርግጠኛ ነሽ? ጊዜ ወስደሽ አስበሽበታል?" "በሚገባ" አለች ሳታስጨርሰኝ። ከዛ በኋላ መታገስ አልቻልኩም። "እሺ፤ በሃሳብሽ ተስማምቻለሁ። ተለያይተናል።" ብዬ አስተናጋጇን በምልክት ሂሳብ እንድታመጣ ነገርኳት። በዛው ቅጽበት ከፊቷ ላይ የነበረው ልበሙሉነት ግራ ለመጋባት ቦታ ሲለቅ ታየኝ። ምናልባት ከምሰጣት ፍቅር የተነሳ ዬትም አይሄድም በሚል እሳቤ የተሳሳተ ስሌት አስልታ ይሆን? "በቃ?" አለች "ምኑ?" አልኳት፤ የምር ግራ ገብቶኝ። "ለምን ማቆም እንደፈለኩ እንኳን አጠይቀኝም?" "ምን ያደርግልኛል?" ስላት ግራ ከመጋባት ወደ መብገን ተሸጋገረች። ግን እውነት የእርሷ ምክንያት ምን ያደርግልኛል። "ፍቅረኛህ ተነስታ ማቆም እፈልጋለሁ ስትልህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ መጠየቅ የለብህም?" "መሄድ መፈለግሽ በቂ ነው፤  መሄድ መፈለግሽ በራሱ አንቺን ለመሸኘት ከበቂ በላይ ምክንያት ነው። ሌላ ምክንያት ምን አያስፈልግም።" "አየህ ወሳኔዬ ትክክል ነበር፤ መጀመሪያውኑም አትወደኝም ነበር፣ እንጂ ብትወደኝ ኑሮ እንደዚህ አትመልስልኝም ነበር።" አይደል? አንቺ ስለምትወጂኝ ነው ከመሬት ተነስተሽ እንለያይ ያልሽኝ? ልላት አሰብኩና አላስፈላጊ ንትርኩ ውስጥ ላለመግባት መልሼ ተውኩት "ስላለፈው መነታረኩ አሁን ምን ያደርግልና?" ጠየኳት ቀዝቀዝ ብዬ። "ማለት?" "አቁመን የለ፤ ስለ ቀደመው ነገር ማውራት አስፈላጊነቱ አልታየኝም።" ራሷን ወደ ጎንና ጎን አነቃነቀችው። ምን ማለቷ ይሆን? መበሳጨት እንደጀመረች አተነፋፈሷ ብቻውን ያሳብቅ ነበረ። አይኖቿን አተኩሬ ተመለከትኩ፤ በመልካሙ ዘመን የሰጠችኝ ፍቅርና እንክብካቤ ታወሰኝ፤ ቢያንስ አንድ ውለታ መዋል እንዳለብኝ ተሰማኝ። እና በስሟ ጠራኋት፤ ሳላቆላምጣት። "አቤት" "ምኔም ካልሆነች ሴት ጋር ከዚህ በላይ መቀመጥ አልፈልግም፤ አብረንም አንወጣ ነገር የአብሮነት ጉዟችንን ጨርሰናል። እናም እዚህ ጎልቼሽ ጥዬሽ ከምሄድ፤ ከእነ ክብርሽ አንቺ ቀድመሽ ትሄጂ?" አልኳት አስተናጋጇ ሂሳቡን አስቀምጣ እንደተመለሰች። በግርምት ትክ ብላ አየችኝ፤ እይታዋ "ጨካኝ ነህ" ያለኝ መሰለኝ። አያችሁልኝ ደግነቴ በክፋት ሲወሰድ። በእርግጥ እንድታመሰግነኝ አልጠብቅም፤ አዎ መልካምነት ለራስ ነው። አይኖቿ እንባን ማቃር ጀምሩ "ታሳዝናለህ እሺ፤ በጣም" ብላ ተነስታ እየተጣደፈች ወጣች። ምን እንዳናደዳት ግን አልገባኝም። "እኔን ትተሽኝ እንድትኖሪ አልፈቅድልሽም!" ብዬ መደንፋት ነበረብኝ? ወይንስ "ካላንቺ መኖር አልችልም" ብዬ መነፍረቅ? መውደድ እኮ ከወደዱት ጋር የግድ አብሮ መዝለቅ ላይሆን ይችላል። መውደድ የወደዱትን ሰው ሃሳብ ማክበርና መቀበልም ነው። በእርግጥ መውደድ የራስ ተመን ዝቅ ባደረገ ግንኙነት ውስጥ ላለመዝለቅ ለራስ መቆምንም ይጨምራል። እኔም ያደረኩት ይሄንኑ ነው። እዛው እንደተቀመጥኩ ስልኬን አውጥቼ "ሌላ" ቦታ መደወል ጀመርኩ። አዎን "ሌላ" ቦታ። ውስጤ "የ'singleness ትሩፋት" ሲል ተሰማኝና ፈገገ አልኩ። ልብ ወለድ✍️ https://t.me/Yeroreflect

July 20, 2025 305 5