በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ #ሰኔ_24_ቀን_የሚከበሩ_ዓመታዊ_የቅዱሳን_በዓላት #እንኳን_አደረሳችሁ #ቅዱስ_ሙሴ_ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) =>ግብጻውያን ስማቸውን ጠርተው ከማይጠግቧቸው ቅዱሳን መካከል አንዱ ኢትዮዽያዊው አባ ሙሴ ጸሊም ነው:: በእኛ ኢትዮዽያውያን ግን ይቅርና በወርኀዊ በዓሉ (በ24) በዓመታዊ በዓሉ እንኩዋ ሲከበር ብዙም አይታይም:: =>ቅዱሱ ሰው በትውልዱ ኢትዮዽያዊ ሲሆን ያደገውም እዚሁ ሃገራችን ውስጥ እንደሆነ ይታመናል:: ገና በወጣትነቱ አገር የሚያሸብር ሽፍታ ነበር:: ሙሴ ጸሊም ወደ ግብጽ የሔደበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም መምለክያነ ጣዖት (ፀሐይን ከሚያመልኩ ሰዎች) ጋር ይኖር ስለ ነበር ምናልባት እነርሱ ወስደውት ሊሆን ይችላል:: ቅዱስ_ሙሴ በምድረ ግብጽም በኃይለኝነቱ ምክንያት የሚደፍረው አልነበረም:: ፀሐይን ያመልካል: እንደ ፈለገ ቀምቶ ይበላል: ያሻውን ሰው ይደበድባል:: ነገር ግን በኅሊናው ስለ እውነተኛው አምላክ ይመራመር ነበርና አንድ ቀን ፀሐይን "አምላክ ከሆንሽ አናግሪኝ?" አላት:: እርሷ ፍጡር ናትና ዝም አለችው:: ቅዱስ ሙሴ ምንም አስቸጋሪ ሰው ቢሆንም ፈጣሪን መፈለጉን ግን ቀጥሏልና አንድ ቀን ተሳካለት:: መልካም ክርስቲያኖችን አግኝቶ ወደ ገዳመ_አስቄጥስ ቢሔድ በዛ ያሉ መነኮሳት ወደ እውነት እንደሚመሩት ነገሩት:: እርሱም ሰይፉን እንደታጠቀ ወደ ገዳም ገባ:: መነኮሳቱ ፈርተውት ሲሸሹ ታላቁ አባ_ኤስድሮስ ግን ተቀብለው አሳረፉት:: "ምን ፈለግህ ልጄ?" አሉት:: "እውነተኛውን አምላክ ፊት ለፊት ማየት እፈልጋለሁ" የሙሴ ጸሊም መልስ ነበር:: አባ ኤስድሮስም "የማዝህን ሁሉ ካደረግህ ታየዋለህ" ብለው ወደ መነኮሳት አለቃ ቅዱስ_መቃርስ_ታላቁ ወሰዱት:: መቃሬም ክርስትናን አስተምረው አጠመቁትና ለአባ ኤስድሮስ መለሱላቸው:: ከዚህ ሰዓት በሁዋላ ነበር የአባ ሙሴ ጸሊም ሕይወት ፍጹም የተለወጠው:: በጻድቁ እጅ ምንኩስናን ተቀብሎ ይጋደል ጀመር:: በጠባቧ በር ይገባ ዘንድ ወዷልና ያ በሽፍትነት የሞላ አካሉን በገድል አረገፈው:: ከቁመቱ በቀር ከአካሉ አልተረፈለትም:: ወገቡን በአጭር ታጥቆ መነኮሳትን አገለገለ:: አጋንንት በቀደመ ሕይወቱ በሕልም: አንዳንዴም በአካል እየመጡ ይፈትኑት ነበር:: እንዳልቻሉት ሲረዱ ተሰብስበው መጥተው በእሳት አለንጋ ገርፈው አቆሳስለውት ሔዱ:: እርሱ ግን ታገሰ:: በበርሃ ለሚኖሩ አበው መነኮሳት ሁሉ ብርሃን በሆነ ሕይወቱ ሞገስ ሆነላቸው:: ለኃጥአን ደግሞ መጽናኛ ሆነ:: በተራራ ላይ ያለች ሃገር ልትሠወር አይቻላትምና ስም አጠራሩ በመላው ዓለም ተሰማ:: ሁሉም "ሙሴ_ጸሊም ይል ጀመር ፡፡ በየበርሃው ያሉ አበው ብቻ ሳይሆነ ዓለማውያን መኩዋንንት ሳይቀሩ ሊያዩት ይመኙ ነበር:: እርሱ ግን ራሱን "አንተ ጥቁር ባሪያ ስለ ኃጢአትህ አልቅስ" እያለ ይገስጽ: ከውዳሴ ከንቱም ይርቅ ነበር:: ከቆይታ በኋላም በመነኮሳት ላይ እረኛ (አበ ምኔት) ሆኖ ተሾመ:: እንደሚገባም አገለገለ:: የበርካቶችን ሕይወት ጨው በሆነ ሕይወቱና ምክሩ አጣፍጦ: ድርሳናትንም ደርሶ እያረጀ ሔደ:: ከቁመቱ መርዘም የጽሕሙ ነጭነትና አወራረዱን ያዩ ሁሉ ሲያዩት ያደንቁት ነበር:: በመጨረሻም በ375 ዓ/ም በርበረሮች (አሕዛብ) ገዳመ አስቄጥስን ሲያጠፉ ሌሎች መነኮሳት ሸሹ:: እርሱ ግን አልሸሽም ብሎ ከ7 ደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚሕች ቀን ተሰይፎ በሰማዕትነት አልፏል:: =>ቅዱስ ሙሴ ጸሊምን ለርስቱ ያበቃ ጌታ ለእኛም ዕድሜ ለንስሃ: ለዘመን ለፍስሃን አይንሳን:: ከበረከቱም ፈጣሪው ያድለን:: => #ሰኔ_24_ቀን_የሚከበሩ_ዓመታዊ_የቅዱሳን_በዓላት 1.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም (ኢትዮዽያዊ) 2."7ቱ" ቅዱሳን መነኮሳት (ደቀ መዛሙርቱ) 3.አባ ኤስድሮስ ታላቁ ❖ #ወርኃዊ_በዓላት 1፡ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት 2፡ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ 3፡ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ 4፡ ቅዱስ አጋቢጦስ 5፡ ቅዱስ አብላርዮስ 6፡ አቡነ ዘዮሐንስ ዘክብራን 7፡ ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ => መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል:: ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ "የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ" ይላቸዋል:: እላችሁአለሁ: እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል:: (ሉቃ. 15:3-7) << " #ወስብሐት_ለእግዚአብሔር ">>
ጸሎት የሁሉም ነገር ቁልፍ ነው።✝️🤲🙏🛐: post #1908 — TG.ME
June 30, 2026 1.8K 5