ጷጉሜን ከስራ እረፍት በማድረግ የፌስቲቫል ወር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተነገረ
በጳጉሜ አብ ፌስቲቫል ማህበር አማካኝነት ላለፉት 8 ዓመታት በደማቅ ሁኔታ ሲካሄድ የቆየዉ የጷጉሜ ፌስቲቫል ዘንድሮም ለየት ባለ ሁኔታ ለ9ኛ ጊዜ ጷጉሜ የአፍሪካ ወርቃማ ወር በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ህብረት ግቢ ዉስጥ ከጷጉሜ 2 እስከ 5 እንደሚካሄድ ተገልጿል ።
የኢትዮጵያዉያን ብቻ በሆነዉ ጷጉሜ ወር የሚካሄደዉ ይህ ፌስቲቫል ሀገራችንን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ የእርስ በርስ ትስስር ማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዋናዉ ዓላማ መሆኑን የጳጉሜ አብ ፌስቲቫል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሃይለአብ መረሳ መናገራቸዉን ብስራት ሬዲዮ ሠምቷል ።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ አመጋገብ ፣ጭፈራ እንዲሁም እንደ ደራሮ ፣እሬቻ እና ሬራና የመሳሰሉ የአዲስ ዓመት አከባበር ስነ ስርዓቶችን ጨምሮ በርካታ ዝግጅቶችን በፌስቲቫሉ ላይ ለሚታደሙ እንግዶች ፣ቱሪስቶችና ተሳታፊዎች ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉ ተጠቁሟል ።
ጷጉሜ ወርን ከስራ እረፍት በማድረግ የፌስቲቫል ወር እንዲሆንና በዩኔስኮ ላይ 13ኛዉ ወር በዓለም ላይ ብቸኛ እንደመሆኑ ለማስመዝገብ የሚቻልበትን ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል ።
ጷጉሜ 1 ለሰላምና ለፍቅር ፣ጷጉሜ 2 ለባህልና ለአፍሪካ አንድነት ፣ጷጉሜ 3 ጷጉሜ ለልጆች ፣ጷጉሜ 4 እንነግድ በጷጉሜ እና ጷጉሜ 5 የተፈጥሮ ዉበታችን ለቱሪዝም መስህብ በሚል መሪ ቃል ፌስቲቫሉ ይካሄዳል ።
በእያንዳንዱ ቀን የተለያዩ በአይነታቸዉ ልዩ የሆኑ ዝግጅቶች እንደሚካሄድ ጳጉሜ አብ ፌስቲቫል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አስታውቋል ።
August 25, 2026 54