ይህን ጥያቄ ሳንመልስ “የዜጎች ቀይ መስመር” በሚል አገላለጽ የውይይት በሮችን ለመዝጋት መሞከር ከመፍትሔ ይልቅ ግጭትን ሊያሰፋ ይችላል።
መፍትሔው፡ የጋራ አስተዳደር ማዕቀፍ
በእኔ እይታ፣ ለዚህ ውስብስብ ጉዳይ ሊቀርብ የሚገባው መፍትሔ የሚከተሉትን አራት እውነቶች በአንድ ማዕቀፍ ማስተናገድ የሚችል መሆን አለበት:-
1. አዲስ አበባ የፌዴራል ዋና ከተማ መሆኗ፤
2. የከተማዋ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው፤
3. አዲስ አበባ ከኦሮሞ ሕዝብና ከክልሉ ጋር ያላት ታሪካዊ እና ነባራዊ ትስስር፤
4. በከተማዋና በኦሮሚያ መካከል የውኃ፣ የመሬት፣ የትራንስፖርት፣ የገበያ፣ የአካባቢ ጥበቃና የከተማ መስፋፋት ጉዳዮችን የሚያስተዳድር ዘላቂ የጋራ ማዕቀፍ።
ይህ አንዱን በሌላው ላይ አሸናፍ በማድረግ የሚገኝ መፍትሔ አይደለም። የሁለቱም ሕዝቦችና መስተዳድሮች ዕጣ ፈንታ በጥልቅ የተሳሰረ በመሆኑ፣ በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ የሁለቱን ጥያቄዎች ማስማማት ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው። ስለዚህ ተገብው አካሄድ በቀይ መስመር መለየት ሳይሆን በቀይ ምንጣፍ በደንብ ማገናኘት ነው።
ቀዩ መስመር ግን ለማነው?
በመጨረሻ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ይቀራል፦ “ቀዩ መስመር ለማን ነው? አስማሪዎቹስ ማን ናቸው?”
“አዲስ አበባ የዜጎች ቀይ መስመር ነች” የሚለው አገላለጽ በመሠረቱ በራሱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በሀገራችን ሁሉም ዜጎች እኩል ከሆነ፣ ይህ ቀይ መስመር በውስጥ ለማነው የሚሰመረው? ለኦሮሞ ሕዝብ ከሆነ፣ ኦሮሞን ከየትኛው ዜጋ ለመለየት ነው? ነው ወይስ አሁንም በዜጎች መካከል ደረጃ አለ?
የኦሮሞን ታሪክ፣ መብትና ሕገ-መንግሥታዊ ጥቅምንስ በውል ሳንመረምር ቀይ መስመር ማስመሩስ ተገብ አካሄድ ነው? የምክክር ባህልስ የተዘጋ መደምደሚያ ይዞ ወደ ጠረጴዛ በመምጣት ይዳብራል?
የሆነው ሆኖ እውነተኛ መፍትሔ የዜጎችን እኩልነት፣ የከተማዋን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የኦሮሞን ታሪካዊ ትስስርና የኦሮሚያን ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ በአንድ ላይ የሚያከብር መሆን አለበት።
አዲስ አበባን የሁላችንም ለማድረግ የአንድን ሕዝብ ታሪክ እንዳልነበረ ማድረግ አያስፈልግም፤ እንዲያውም አደገኛ ነው። የዜጎች እኩልነት ማለትም የተለያዩ ታሪኮችንና ነባራዊ ሁኔታዎችን መካድ አይደለም። እኩልነት በተቃራኒው፣ እነዚህን ልዩነቶች በፍትሃዊ መንገድ መረዳትና ማስተናገድ ነው።
ስለዚህ ዛሬ የሚያስፈልገን “አዲስ አበባ የማን ናት?” በሚል የማያልቅ የባለቤትነት ክርክር ውስጥ መዳከር ሳይሆን፣ “የሁላችንንም መብት የሚያረጋግጥ የአዲስ አበባ የአስተዳደር ሞዴል ምንድነው?” የሚል ብልህ የሕግና የፖሊሲ ምርምርና ውይይት ነው።
ዘላቂው መንገድ በፍራቻ ስሜት የተነዳ የባለቤትነት ፖለቲካ አይደለም። በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በሕግና በተግባራዊ አስተዳደር ላይ የተመሠረተ የጋራ መፍትሔ ነው።
በእኔ እይታ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መካከል መቀመጥ ያለበት ቀይ መስመር ሳይሆን፣ በመከባበር፣ በፍትሕና በውይይት የተዘረጋ ቀይ ምንጣፍ ነው።
Via - Birhanu M Lenjiso (phd)
August 24, 2026 38