ከነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ባህርያት
****
1. የሥራና የአምልኮ ሰው ናቸው፤ ሌትም ሆነ ቀን ዕረፍት የላቸውም፡፡
2. እጅግ ቸርና እጅግ ለጋስ ናቸው፡፡
3. ታጋሽና ቁጥብ፣ ጨዋና ራሳቸውን የገዙ ናቸው፡፡
4. ያገኙትን ሰው በሰላምታ ይቀድማሉ፡፡
5. ያለ ጉዳይ ወይም ያለምክንያት አይናገሩም፡፡
6. ሲናገሩ በዝርዝር ሳይሆን ጠቅላይ በሆኑ ቃላቶች ነው፡፡
7. የአላህን ፍጥረታት በመመልከት ድንቅ ተዓምራቱን ዘወትር ያስተነትናሉ፡፡
8.ለዓለማት ህዝብ ሁሉ መስተካከል ያስባሉ ይጨነቃሉ፡፡
9. ከኩራት፣ ከመመፃደቅና ከጉራ የራቁ ናቸው፡፡
10. ዝምታ ያበዛሉ፡፡ ሀሳብ ትካዜያቸው ተከታታይ ነው፡፡
11. ገፍታራና ኮስታራ አይደሉም፡፡ በሻሻ ናቸው፡፡
12. ላያቸው ሁሉ የሚስብ ግርማ ሞገስ አላቸው፡፡
13. ትንሿን የአላህ (ሱ.ወ.) ፀጋ እንደ ትልቅ ያያሉ፡፡
14. ከበሉም ሆነ ከጠጡ በኋላ ሁሌም ያመሰግናሉ፡፡
15. አላህ (ሱ.ወ.) ከሰጣቸው ነገር አንድንም ነገር አያጣጥሉም፡፡ አይንቁም፡፡
16. ለራሳቸው ስሜት ብለው አይቆጡም፤ ለራሳቸው አይሞግቱም፡፡
17. ሁለመናቸውን ለአላህ ያሳደሩ ባርያው ናቸው፡፡
18.ለሐቅ ሲሉ ይቆጣሉ፡፡ ሐቅን እስኪያነግሱ ድረስም ዕረፍት የላቸውም፡፡
19. የተቆጡ እንደሆነ ከቦታው ዘወር ይላሉ፡፡
20. ሲደሰቱ ዐይናቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ድል ሲያገኙ አምላካቸውን ማመስገን ያበዛሉ፡፡
21. ሳቃቸው አብዛኛውን ጊዜ ፈገግታ ነው፡፡
22. ወደቤታቸው ሲገቡ ጊዜያቸውን ለሶስት ይከፍላሉ፡፡ ለአላህ፣ ለቤተሰባቸውና ለራሳቸው፡፡
23. ሰዎች እንዲዋድዱ ይመክራሉ፤ የተጣላን ያስታርቃሉ፤ ግንኙነታቸው ተመልሶ እንዲጠናከር ያደርጋሉ፡፡
24. የማህበረሰቡ ክብር የሚሰጠውን ሰው ያከብራሉ፡፡ በህዝቦቹ ላይም ሀላፊነት ይሰጡታል፡፡
25. ስለ ሰሓቦቻቸው ሁኔታ ይቃኛሉ፡፡ የቸገረውንና የጠፋውን ይጠይቃሉ፡፡
26. መልካምን ነገር መልካም፤ መጥፎን ነገር መጥፎ ይላሉ፡፡
27. በነገራቸው ሁሉ መካከለኛና ሚዛናዊ ናቸው፡፡
28. በዲን ጉዳይ ላይ ጽንፈኝነትም ሆነ ቸልተኝነት የለባቸውም፡፡
29. ሲታጠቡ፣ ሲለብሱ፣ ሲጫሙ፣ ፀጉራቸውን ሲያበጥሩ እንዲሁም ሌሎች መልካም ነገሮችን ሲሰሩ ቀኛቸውን ያስቀድማሉ፡፡
30. ሰሐቦቻቸው እንዳይዘናጉ ብለው በየጊዜው ይመክሯቸዋል፣ ይገስጿቸዋል፡፡
31. ሁሉንም ነገር እአላህ እንደፈቀደው ይቀበላሉ፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) የሻላቸውን ይወዳሉ፡፡ እሱ የመረጠላቸውንም ሳይቆረቁራቸው ይቀበላሉ፡፡
32. የሕዝበ ሙስሊሙ መሪ ቢሆኑም ለየት ያለ ዙፋንም ሆነ መቀመጫ የላቸውም፡፡ አጃቢ ባንድም ሆነ ጠባቂ ሰራዊት አልነበራቸውም፡፡
33.ደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ ነው የኖሩት፤ የቤቶቻቸው ጣሪያም ቅርብ ነው፡፡
34. አብዛኛው ምግባቸው ተምርና ውሃ ነው፡፡
35. በማኀበራዊም ሆነ የትግል ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ አላቸው። በከዕባ ዕድሳት ወቅት፣ የመዲና መስጂድ ሲገነባ፣ በኸንደቅ ምሽግ ቁፋሮ ጊዜ ትልቅ እገዛ አድርገው ነበር፡፡
36. ይበልጥ ወዳጆቻቸው የነበሩት በአምልኮ ተግባራት በላጮች የሆኑት ናቸው፡፡
37. እርሳቸው ዘንድ ምርጡ ሰው ለሰው ጠቃሚ የሆነ፣ ለሌሎች የሚያስብና ሌሎችን የሚያግዝ ነው፡፡
38. አላህን (ሱ.ወ.) ያወሱ ቢሆን እንጂ አይቆሙም፤ አይቀመጡም፡፡ አይተኙም፣ አይነሱም፡፡
39.ሰዎች ስብስብ ዘንድ በመጡ ጊዜ በበቃቸው ቦታ ላይ ነው የሚቀመጡት፡፡ ሰሓቦቻቸውንም በዚሁ ሥርዓት ያዙ ነበር፡፡
40. የተቀመማጧቸውን ያለ ልዩነት ያናግራሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው እኔን ነው የሚወዱት ብሎ እስኪያስብ ድረስ አንዱን ከሌላኛው ላይ ሳይለዩ ያቀርባሉ፡፡
500 የነቢዩ ሰ.ዐ.ወ ባህርያት መጽሐፍ
ነጃሺ ማተሚያ ቤት
ትርጉም ፦ ሙሐመድ ሰዒድ (ABX)
https://t.me/Nejashipp
Telegram
Nejashi Printing Press
ይህ የነጃሺ ማተሚያ ቤት ኦፊሻል የቴሌግራም ቻናል ነው። የተለያዩ ጠቃሚ መልዕክቶችን፣ አዳዲስ የህትመት ውጤቶቻችንና አገልግሎቶቻችንን ተከታተሉን፣ ለሌላውም ሼር አድርጉ።

August 18, 2026 4.2K 45