Ethio engineering Group: post #3811 — TG.ME

ጥቅምት 12/2018 ዓ/ም(ኢኢግ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የግሩፑ ዋና መ/ቤት በመገኘት አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ላይ የመስክ ምልከታ አካሄዱ።

በዚሁ ወቅት የግሩፑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኮ/ል ሸጋው ሙሉጌታ ባለፉት አምስት አመታት በግሩፑ ተመርተው በሀገሪቱ የተሰራጩ ምርቶችን አቅርበዋል። በተጨማሪም የ2018 በጀት አመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ አመት የስራ አፈፃፀም ላይ ገለጻ አቅርበዋል።

ግሩፑ ተኪ ምርቶችን በማምረት፣ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን ከፍተኛ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት አመት በዝግጅት ምዕራፍ ቀደም ሲል የተዘጋጁ መመሪያዎችን መከለስ፤ ለፋብሪካዎች የግብአት ዝግጅት ማካሄድ፣ የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከግሩፑ ሰራተኞች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የተለያዩ የስራ ክፍሎችንም ጎብኝተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ መልስ ግሩፑ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ እና ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

በእቅድ ላይ የውል ስምምነት መፈረሙ ሁሉም እቅዱን በደንብ እንዲያውቅ ያደረገ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸው ከዚህም ባሸገር የሃላፊነት እና የተጠያቂነት አሰራር እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል፡፡
በግሩፑ ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር አንፃር በዋናው መ/ቤት የተከናወነው የሪ ኢኖቬሽን ስራ፣ የአመራሩና ሰራተኛው ቅንጅት እና ቁርጠኝነት ፣የህፃናት ማቆያ ማእከል ስራ እና ጤና ጣቢያ በተደራጀ መልኩ አገልግሎት መስጠቱ ጠንካራ ጎን መሆኑን አንስተዋል።
የግሩፑን የምርምር ዘርፋን ማጠናከር ፣ የተቋሙን ኦዲት ሪፖርት ማጥራት፣ ኢ አር ፒን ሙሉ በሙሉ መተግበር፣ እንዲሁም ከህግ አንፃር የተያዙ ጉዳዮች እልባት እንዲገኙ ማድረግ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ የተባሉ ናቸው።በዚህ ረገድ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መለሰ መና በማጠቃለያ ንግግራቸው ግሩፑ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ዕቅዶችን ማሳካት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተቋሙ ህልውና በጊዜ እና በጥራት ማምረት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ሊተኮርበት ይገባል ብለዋል፡፡

የደንበኛ እርካታን ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያግዙ አሰራሮችን ማዘመን ፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪትን ማረጋገጥ፣ የግሩፑን አደረጃጀት በማጠናቀቅ ወደ ተግባር ማሸጋገር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በግሩፑ ስር የሚገኘውን አዲሰ ማሽንና መለዋወጫ ማምረቻ ኢንዱሰትሪንም ጉብኝተዋል።
October 23, 2025 1.9K 4