M️ETANOIA: post #451 — TG.ME

ፀሓይ እየጋለች ነው። ኢየሱስ የመስቀሉን ዕንጨት ተሸክሞ እየታገለ ነው። ተጠምቷል። ብዙ ደም ፈስሶታል። በሕመም እየተሠቃየ ነው። መስቀሉን የሚሸከምበት ዐቅም አልነበረውም። ኢየሱስ ወደ መሰቀያው ቦታ ሳይደርስ እንዳይሞት የመቶ አለቃው ሳይሠጋ አልቀረም። ሮማውያን ወታደሮች ማንንም የጕልበት ሥራ ለማዘዝ ሥልጣን አላቸውና የቀሬናው ስምዖን የመስቀሉን ዕንጨት እንዲሸከም አስገደዱት (ማቴ. 27፥32፤ ሉቃ. 23፥26)። ወታደሮቹ ይህን ሲያደርጉ ለኢየሱስ አዝነውለት ሳይሆን፣ መንገድ ላይ ከሚሞት ከነሕይወቱ ለመሰቀል እንዲደርስላቸው ነው። ሁኔታው፣ ጌታ ኢየሱስ መስቀሉን ተሸክሞ በበርካታ ሥዕሎች ላይ የሚታየውን አይመስልም። መስቀሉ ሙሉ በሙሉ የሚሸከሙት አይደለምና። ቋሚውና አግዳሚው ተጋጥመው የሚዘጋጀው ሙሉው መስቀል ላልተገረፈ ሰው እንኳ ከባድ ነው። ስለዚህ ለመሰቀል የሚወሰዱ ፍርደኞች አግዳሚውን ብቻ ነው የሚሸከሙት። ያ ብቻ ከ22-31 ኪሎ ግራም ሊመዝን ይችላል። አግዳሚው በጫንቃው ላይ እንዲጋደም ይደረግና የሚሰቀለው ሰው እጆቹ ተዘርግተው በዚያ ላይ ይታሰራሉ። ተሸካሚው ከሸክሙ ክብደት የተነሣ ወደፊት ያዘነብላል። ጌታ ኢየሱስና የቀሬናው ስምዖን የመስቀሉን አግዳሚ በዚህ መልኩ በየተራ ተሸክመው ወደ ጎልጎታ ሄደዋል። ቋሚው የመስቀሉ ዕንጨት ግን ቀደም ተብሎ ወደዚያ የተወሰደ፣ እንዲያውም በዚያ ተተክሎ የሚቈይ ነው። በዚህ ዐይነት እየተጓዙ “የራስ ቅል” የሚል ስያሜ ወዳለው ጎልጎታ ተብሎ የሚታወቅ ስፍራ ደረሱ። “የራስ ቅል” የሚል ትርጓሜ ለጎልጎታ የተሰጠው ሮማውያን የሞት ፍርድ የሚፈጽሙበት ዕውቅ ቦታ ስለሆነ፣ ወይም መልክዐ ምድሩ የራስ ቅል ስለሚመስል ወይም በርካታ መቃብሮች በስፍራው ስለሚገኙ ሊሆን ይችላል። የአይሁድ ትውፊት መነሻው እንደ ሆነ የሚነገርለት ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላ ክርስቲያናዊ ትውፊትም አለ። ይኸውም፣ ጎልጎታ አዳም የሞተበትና የተቀበረበት ስፍራ መሆኑ ነው። ከዚህም የተነሣ ከመስቀሉ ግርጌ የአዳምን የራስ ቅልና ጥቂት ዐጥንቶችን የሚያሳዩ በርካታ የመስቀል ምስሎች አሉ። አዳም እዚያ ይሙትም አይሙት፣ የክርስቶስ ሞት አዳም ያመጣብንን ሞት ስላሸነፈ የጥንት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንት ትውፊቱን ይጠቅሱታል። የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለማዋረድና ዝናውን ለማበላሸት ይፈልጉ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን በመካከል አድርገው፣ “ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ”። ይሄ የመስቀሉ ውርደት አካል ነው። ይህን ሲያደርጉ ግን ሳያውቁት በኢሳይያስ 53፥12 የተነገረውን ትንቢት ፈጽመዋል። ማርቆስ እንደ ተናገረው፣ “መጽሐፍም፦ ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ ያለው ተፈጸመ” (15፥27-28)። በርግጥ ከዐመፀኞች ጋር የተቈጠረው በመስቀሉ ላይ ብቻ አልነበረም፤ ከዚያ በፊትም “የኀጢአተኞች ወዳጅ” እየተባለ ነቀፋ ሲቀርብበት ነበርና (ማቴ. 11፥19፤ ሉቃ. 7፥34)። ኢየሱስ ንጹሕ፣ ሞቱ ግን የወንጀለኛ ነው። እናም ገላው በደም አበላ እንደ ተነከረ፣ ፊቱ በጭንቅ እንደ ተኰማተረ እንደ ወንጀለኛ ተሰቀለ። ተመልካቹ ሁሉ አግልሎታል፤ በሃይማኖተኞቹ እና በእርሱ መካከል፣ በክቡራን እና በእርሱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የተረገመ፣ የተጠላ መሆኑ ይታሰባል። ኢየሱስ ንጹሕ ነው፤ ሞቱ ግን የዐመፀኛ። በሮሜ ላይ ፀመፅ እንዲነሣ እየቀሰቀሰ አልነበረም፤ ነገር ግን ሮሜ በመደበኛነት በዐማፅያን ላይ የምታወርደውን መከራ ተቀበለ። ሊመጣ ያለውን መከራ ለሕዝቡ አስጠነቀቀ፤ ከዚያም ወደፊት ሄዶ መከራውን ተቀበለ። የተሰቀለው ገጽ 125-126።

❤15🙏2👍1🔥1
April 11, 2026 1.2K 7