‹‹ክላስ ሲኖረኝ ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ያው መስጂድ ካልሆንኩ ቤት ነኝ፡፡››
‹‹ከኛ ክላስ ውጪ ስንት ክላስ ታስተምራለህ?››
‹‹ሁለት››
‹‹ዕሮብ እና ሰኞ ጠዋት ላይ ክላስ የለንም እና ቤት ትኖራለህ እንዴ?››
‹‹አልኖርም፡፡ በቃ ያኔ መምጣት ትችያለሽ፡፡››
ቀስ እያሉ ጎዳናው ላይ ሲጓዙ ላያቸው ባልና ሚስት ሳይመስሉት አይቀሩም፡፡ ለትንሽ ደቂቃዎች በመካከላቸው ዝምታ ነገሰ፡፡ ቀመር ዝምታውን መስበር ፈለገች፡፡
‹‹እሺ ዛሬ ስለ ሂባ አትነግረኝም?››
‹‹እሱን ብድርሽን ስትከፍዪ እነግርሻለሁ፡፡››
በየመሀሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን እየተጠያየቁ ከኢምራን ትንሿ ቤት ደረሱ፡፡ የግቢው መግቢያ ጋ ሲደርሱ የኢምራን አከራይ ወ/ሮ አርሴ እንጨት እየፈለጡ ነበር፡፡ ከቀመር ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ ወ/ሮ አርሴ ፈገግ ብለው ‹‹ዎይ አምረኔ አበባ ሚትመስል ሚስት አይደል እንዴ ያመጣኸው?›› አሉ፡፡ ቀመር ኢምራንን እያየች ከልቧ ፈገግ አለች፡፡ እሳቸውን አልፈው ወደ ግቢው ገቡ፡፡ ሰፋ ያለ ግቢ ነው፡፡ ወ/ሮ አርሴ የሚኖሩበት ቤት ከሚያከራዩዋቸው ቤቶች የተሻለ አይደለም፡፡ በሩን ከፍቶ ገባና መብራቱን ካበራ በኋላ እንድትገባ ጋበዛት፡፡ቤቱ ውስጥ አንድ ፍራሽ ወለሉ ላይ ከመጋደሙ በዘለለ ብዙ ኮተት የለም፡፡
‹‹ኦው አሪፍ…… ስቶቭ አለህ!›› ቀመር የቤቱ የግራ ጥግ ጋ የተቀመጠውን ስቶቭ እየጠቆመች ፈገገች፡፡ ሰዓቱ በጣም እየሄደ እንደሆነ እየተሰማው ነው፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻቸውን መሆናቸው ሰላም ነሳው፡፡ ቀመር ፍራሹ ላይ ሄዳ ተቀመጠች፡፡
‹‹ፍራሹም አሪፍ ነው ግን አንተ ብቻ የተኛህበት አይመስልም፡፡ ማለቴ ሂባም በሀሳብ አብራህ ሳትንከባለልበት አትቀርም፡፡›› አለችና ቀና ስትል ግድግዳው ላይ የተለጠፈውን ፅሁፍ ተመለከተችና ጮክ ብላ አነበበችው፡፡ ‹‹ሴት ልጅ እናትህ ስትሆን አማራጭ ስለሌላት ነው ፣ እህትህም ስትሆን ተፈጥሮ አስገድዷት ነው። ሚስትህ ስትሆንም ቤተሰቧ ፈርዶባት ነው። አንድም ቀን በራሷ ላይ የመወሰን አቅም የሌላትን አካል አታፍቅር!›› አይኖቿን በምርመራ ጨረር አጅባ አይኑ ላይ ወረወረቻቸው፡፡
‹‹ይኼን አንተ ነህ የፃፍከው?››
ፅሁፉን ባታየው ደስ ይለው ነበር፡፡ አይኑን መሬት ላይ እየተከለ ‹‹አዎ›› አላት፡፡
‹‹እና ክፍል ውስጥ ከምትለው ጋር አይጋጭም?››
‹‹አይጋጭም እንደውም ተመጋጋቢ ነው፡፡››
‹‹ኦው ሂባ›› ፈገገች፡፡ በልቧ ሚስጥሩን የማወቅ ፍላጎቷ ንሯል፡፡ ግን ዛሬ ይሁን ብላ ልታስጨንቀው አልፈለገችም፡፡
‹‹በቃ ቤቱን አየሽው አይደል ነይ ልሸኝሽ!››
‹‹ኧረ እንግዳ ቤት ገብቶ በባዶ አይሸኝም፡፡››
‹‹ማነው እንግዳ? ኧረ የኔ ቤት ነው እንዳትዪኝ እየፈራሁ ነው፡፡››
‹‹ቤቱማ የአከራይህ ነው ኮተታም››
ከተቀመጠችበት ተነስታ በሩ ጋር ስትደርስ ከነበሩት ሁለት የበር ቁልፎች ውስጥ አንዱን ሰጣት፡፡ ሁለ ነገሯ ያሳሳል፡፡ አንዳንዴ ሂባን በሷ ውስጥ የሚያይ ይመስለዋል፡፡ በልቧ የዚህ ቤት ንግስት ስለመሆን አሰበች፡፡ የምትፈልገው መስመር ላይ በምን መልኩ ማስገባት አንዳለባት በደንብ ታውቃለች፡፡ ጅምሯም እየሰመረ ይመስላል፡፡ ወ/ሮ አርሴን ተሰናብታ ስትጨርስ ወደ ግቢ ሊሸኛት መንገድ ጀመሩ፡፡
ፀሀይ በዚህ መልኩ ወደ ማደሪያዋ ከገባች በኋላ ከሴት ጋር ዎክ አድርጎ አያውቅም፡፡ ልቡ እሷን ቶሎ ሸኝቶ መንገድ ላይ ያለው መስጂድ ገብቶ ለመስገድ ቸኩሏል፡፡ የግቢ በር ጋር ከመድረሳቸው ብዙም ሳይርቅ ተሰናበታትና እየተጣደፈ ወደ መስጂድ ሄደ፡፡ እሷ ልቧ በሀሴት እንደተሞላ ወደ ዶርሟ ተጣደፈች፡፡ እሱ የመቀራረባቸው ጉዳይ እያሳሰበው ነው፡፡ በዚህ መልኩ እንድትቀርበው በመፍቀዱ ይፀፀታል፡፡ ድጋሚ ሴት መቅረብ ፣ ድጋሚ መጎዳት አይፈልግም፡፡
.
ይቀጥላል…
@Lib_Weled
November 29, 2021 5.8K 20