2. በቀሪዉ የዉርስ ሀብት ክፍፍል ላይ ለመሳተፍ የሚፈልግ ወራሽ አስቀድሞ በስጦታ የተቀበላቸዉን ይዞታዎችን ወደ ዉርሱ ሀብት መመለስ አለበት(የሰ/መ/ቁ 249367 ጥር 28 2017 ዓ/ም)፡-ተጠሪ በቀሪዉ የዉርስ ሀብት ክፍፍል ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ከሆነ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 113247 ፣ 160761 ፣ 162475 እና በሌሎችም መዝገቦች በሰጣቸዉ አስገዳጅ ዉሳኔዎች መሠረት አስቀድሞ በስጦታ የተቀበላቸዉን ሁለት ይዞታዎችን ወደ ዉርሱ ሀብት መመለስ አለበለዚያም ከቀሪዉ የዉርስ ሀብት ክፍፍል ዉጭ መሆን ይኖርባቸዋል ፡፡ በመሆኑም ተጠሪ አስቀድሞ በስጦታ ያገኟቸዉን ይዞታዎችን እንደያዙ ቀሪዉን የዉርስ ሀብት ከለሌች ወራሾች ጋር ለመከፋፈል እንደሚችል ገልጸዉ የሚያቀርቡት ክርክርም ሆነ የሥር ፍ/ቤቶች ይህንን ክርክራቸዉን ተቀብለዉ የሰጡት ዉሳኔ የፍ/ሕ/ቁጥር 1065-1067 ግልጽ ድንጋጌዎችንም ሆነ በዚህ ረገድ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከላይ በተጠቀሱና በሌሎችም መዝገቦች የሰጠዉን አስገዳጅ ዉሳኔ የሚቃረን መሠረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው። 3. በፍርድ ቤት በተላለፈ ሰርኩላር መዝገብ ለጊዜው እንዲዘጋ የተሰጠ ትዕዛዝ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑ:-((መ/ቁ.257851 በቀን 25 /04/ 2017 ዓ.ም ) የቀረበለትን ጉዳይ አይቶ የመወሰን የዳኝነት ስልጣን ያለው መሆን አለመሆኑን አይቶ የመወሰን ስልጣን ያለው ጉዳዩን የያዘው ችሎት ፤ ወይም ጉዳዩ በይግባኝ ወይም በሰበር የቀረበለት ችሎት እንጂ በተመሳሳይ ጉዳይ ተፈጻሚ እንዲሆን ትዕዛዝ ወይም በሰርኩላር መመሪያ ሊሰጥ የሚችልበት አግባብ አለመኖሩን ፤ ችሎትም አስተዳደራዊ የሆነውን ሰርኩላር (መመሪያን) መሰረት በማድረግ የቀረበለትን የዳኝነት ጥያቄ አላስተናግድም በማለት የሚሰጥ ውሳኔ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 79(2 እና 3) ስር ከተመለከተው የዳኝነት ነፃነትን ጋር የሚጣረስ ፤ የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል ከሚለው ብሂል አንፃር ሲታይ በኢ.ፌ.ዳ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 37 ስር የተመለከተውን ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚገድብ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው በማለት የሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰበር መዝገብ ቁጥር 247494 ላይ የሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ የሚጥስ ነው፡ 4. ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት፣በመፍጠር ወይም በመገልገል የወንጀል ክስ ሲቀርብ የተገለገለዉ ሰነድ ሀሰተኛ እንደሆነ እና ሀሰተኛ ሰነድ የፈጠረዉ አመልካች መሆኑ በተገቢዉ ማስረጃ መረጋገጥ አለበት(የሠ/መ/ቁጥር 247213 ጥቅምት 05ቀን 2017 ዓ)፡- ጉዳዩ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት፣በመፍጠር ወይም በመገልገል የወንጀል ክስ ሲቀርብ ሰነዱ ሀሰተኛ አይደለም የሚል ክርክር ሲቀርብ ሰነዱ ሀሰተኛ መሆን አለመሆኑ የሚረጋገጥበትን አግባብ የሚመለከት ነው፡፡በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ማንኛዉም ሰዉ የሌዉን ሰዉ መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰዉ ተገቢ ያልሆነ ማናቸዉም መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ መንግሥታዊ ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀት ወይም በመፍጠር ፣ ወደ ሀሰት በመለወጥ ወይም በሐሰተኛ ሰነድ በመገልገል ተጠያቂ የሚሆነዉ በድንጋጌዉ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 3 ስር ተዘርዝረዉ የተጠቀሱትን ማቋቋሚያ ፍሬ ነገሮች (አላባዎች) ተሟልተዉ ሲገኙ ነዉ፡፡እነዚህም አላባዎች፡-ሀ) አንድ መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ጽሁፍ፣ መዝገብ ወይም ማንኛውንም ሰነድ በማስመሰል የተዘጋጀ ወይም የተፈጠረ እነደሆነ፤ ለ) በበመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት መዝገብ፣ በጽሁፍ ወይም በሠነድ የሰፈረን እውነተኛውን ጽሁፍ በመለወጥ ወይም በመደለዝ፣ በሀሰተኛ ፊርማ፣ በእጅ በተደረገ ምልክት ወይም በጣት ፊርማ፣ በማህተም ወይም የሌለውን ሥልጣን ወይም ችሎታ እንዳለው አስመስሎ በመፈረም ሀሰተኛ ሰነድ የተፈጠረ እንደሆነ፤ ወይም ሐ) አንድ ሠነድ በተለይም የፈራሚውን ስም ወይም ፊርማ ወይም የሰነዱን ይዘት፣ አሃዝ፣ ፍሬ ነገር ወይም ዝርዝር መግለጫ በሙሉ ወይም በከፊል በመለወጥ፣ በማሻሻል፣ በመቀነስ ወይም በመጨመር ወይ በማጥፋት ወደሀሰተኛነት ከተለወጠ ወይም ማናቸውንም ሀሰተኛ ፍሬ ነገር ያስገባ ወይም እንዲገባ ያደረገ እንደሆነ እና በዚህ አግባብ ወደ ሀሰት በተለወጠ ወይም በሀሰት በተዘጋጀ ሰነድ እያወቀ የተገለገለበት እንደሆነ የሚሉ ናቸዉ፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አተገባበር ጋር በተያያዘ ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁጥር 241756 ፣245579 እና በሌሎች መዛግብት ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል። 5. ተከሳሽ ሕጻናት ልጆች ካሉት ቅጣት መገደብ ግደታ ነው፡- ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለበት ድንጋጌ ቅጣት እንዲገደብ በህጉ ክልከላ ካልተደረገበት በስተቀር ተከሳሽ ህጻናት ልጆች የሚያስተዳድር መሆኑን ገልጾ ባቀረበበት ፍ/ቤት በህጻናቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ቁሳዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለማስቀረት ሲባል ቅጣቱ ያለመገደብ መሠረታዊ የህግ ስህተት ነው። ሰበር ሰሚ ችሎት = መ/ቁ 282248 /06/02/2017 ዓ/ም 6. በአንድ የቤት ክርክር ላይ ቤቱ በምን ያህል ካሬ ሜትር ላይ እንዳረፉ የቤቱ አቀማመጥ የሚያሳይ እስኬች በባለሞያ ተሰርቶ ቀርቦ መግቢያ መውጫው ተለይቶ ሊፈፀም የሚችል ውሳኔ አለመሰጠቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው። ሰበር መዝገብ =243809 ቀን=07/02/2017 7.የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባዉ ዉሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ወደፊት ለሚሰጡ ዉሳኔዎች ነዉ (የሰ/መ/ቁ 257243 የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ/ም) የሰበር አመልካች እና ሟች የነበራቸዉ ጋብቻ ከ30 ዓመታት በላይ ተለያይተዉ ለየብቻቸዉ የኖሩ መሆኑ ስለተረጋገጠ ጋብቻቸዉ በሁኔታ ፍርሷል ሲል ዉሳኔ የሰጠዉ በወቅቱ በነበረዉ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 20938 ላይ ሚያዚያ 11 ቀን 1999 ዓ/ም በተሰጠ አስገዳጅ የሰበር ዉሳኔ መሰረት ሲሆን ይህ የሰበር ችሎት ዉሳኔ በወቅቱ ተፈጻሚ ሲሆን በነበረዉ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(4) በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት በማናቸዉም ፍርድ ቤት አስገዳጅ ዉሰኔ መሆኑ ግልጽ ነዉ ፡፡ የሰበር አመልካች በፌደሬሽን ምክር ቤት በተሰጠ ዉሳኔ ጋብቻ በሁኔታ ሊፈርስ አይገባም ተብሎ ስለተወሰነ የተሰጠዉ ዉሳኔ ተፈጻሚነት ያለዉ አይደለም የሚል ይዘት ያለዉ ክርክር አቅርበዋል፡፡ ሆኖም ጋብቻ በሁኔታ አይፈርስም ተብሎ በፌደሬሽን ምክር ቤት ከላይ የተጠቀሰዉን የሰበር ዉሳኔን በመሻር ዉሳኔ የተሰጠዉ በ5ኛ የፓርላማ ዘመን አምስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ በመ/ቁ 49/10 ላይ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ስለሆነ ይህ የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባዉ ዉሳኔ ከተሰጠበት መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ ወደፊት ለሚሰጡ ዉሳኔዎች እንጅ ዘጠኝ አመት ወደ ኋላ በመሄድ በ2003 ዓ/ም የተሰጠን ፍርድ የሚሽር አይሆንም፡፡ ስለሆነም የሰበር አመልካች እና የሟች ጋብቻ ሀምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ መጀመሪያ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 04261 በተሰጠ ዉሳኔ ቀሪ የሆነ ነዉ ብለናል፡፡
1