ለእግዚአብሔር_ልጅ_ምሳሌው_የሆነ #ካህኑ_ቅዱስ_መልከጼዴቅ፦ መልከጼዴቅም ዐሥራ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ… — ኩራዝ — TG.ME

                         
#ለእግዚአብሔር_ልጅ_ምሳሌው_የሆነ #ካህኑ_ቅዱስ_መልከጼዴቅ፦ መልከጼዴቅም ዐሥራ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ከአዳም ሥጋ ጋር እንዲልከውና በምድር መካከል እንዲያኖረው እግዚአብሔር ኖኅን አዘዘው እርሷም ቀራንዮ ናት። የዓለም መድኃኒት ክርስቶስም መጥቶ በዚያ እንደሚሠዋ አዳምንም ከልጆቹ ሁሉ ጋር እንደሚያድነው አመለከተው።

ከዚህም በኋላ በአባቱ በኖኅ ትእዛዝ ሤም መልከጼዴቅን በሥውር ወሰደው የእግዚብሔርም መልአክ እየመራቸው ሔደው ወደ ቀራንዮ ተራራም አደረሳቸው መልከጼዴቅም ክህነትን ተሾመ። ዐሥራ ሁለት ደንጊያዎችንም ወስዶ መሠዊያ ሠራ ከሰማይ የወረደለትንም ኅብስትና ወይን መሠዊያ በሠራቸው ደንጊያዎች ላይ መሥዋዕትን አሳረገ።

ምግቡንም መላእክት ያመጡለታል ልብሱም ዳባ ነው በአባታችን አዳም ሥጋ ዘንድ ሲያገለግል ኖረ። አብርሃምም ከጦርነት ነገሥታትን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ኅብስትንና ወይንን አቀረበለት አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው እርሱ ካህንም ንጉሥም ሁኖ ተሹሟልና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በካህኑ ቅዱስ መልከጼዴቅ በአማላጅነቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

                           
#ቅዱስ_ሰራጵዮን፦ ይህም ቅዱስ ሰንዱን ከሚባል አገር ነው። ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውንም ተማረ የዚህንም ዓለም ገንዘብ ሁሉ ትቶ ወደ አረሚ አገር ሔደ ራሱንም በሃያ ብር ሸጦ ማገልገል ጀመረ የሽያጩንም ዋጋ ጠበቀው። እንጀራ ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ ከስሕተታቸው ይመልሳቸው ዘንድ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር።

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ አሳመናቸው ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ ስለርሳቸው ራሱን ባሪያ አድርጎ እንደሸጠ እንጂ እርሱ ባሪያ እንዳልሆነ ነገራቸው ሽያጩንም ለድኆች እንዲሰጡት ሰጣቸው።

ከዚህም በኋላ መንካያውያን ወደሚባሉ ሕዝቦች ሒዶ ለነርሱም ራሱን ሸጠ የክብር ባለቤት ወደሆነ ክርስቶስ እምነት እስከመለሳቸው ድረስ ተገዛላቸው። ከዚህም በኋላ ደግሞ ወደ ሮሜ አገር ሒዶ በሰላም እስከ አረፈ ድረስ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጒሜን 3 ስንክሳር።

                             

                          
#የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መሐለ እግዚአብሔር ወኢይኔስሕ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከጼዴቅ። እግዚአብሔር በየማንከ"። መዝ109፥4-5። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 17፥20-31።

                             
#የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ገሃደይ መጽእ። ወአምላክነሂ ኢያረምም። እሳት ይነድድ ቅድሜሁ"። መዝ 49፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 7፥1-7፣ ይሁ 1፥11-17 እና የሐዋ ሥራ 5፥16-26። የሚነበው ወንጌል ማቴ 25፥31­46። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል በዓል ለሁላችን ይሁንልን
September 7, 2026 79