🕊
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ †
[ ❖ ነሐሴ ፲፰ ❖ ]
† እንኩዋን ለሊቁ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †
[ † 🕊 ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ 🕊 † ]
ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ [የተወለደባት] ግብጽ ናት:: የተወለደው በ፫ [3]ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን በምግባሩ: በትምሕርቱ ለምዕመናን ጥቅም ሆኗቸዋል:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ ቅዱስዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት ሔዷል::
ቅዱስ ዼጥሮስ የግብጽ ፲፯ [17]ኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል:: ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም ፫ [3]ቱ ግን ተጠቃሽ ነበሩ::
፩. ቅዱስ እለእስክንድሮስ [ ደጉ ]
፪. አኪላስ [ ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ ]
፫. አርዮስ [ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ]
ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር ነበር:: አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ: ስለ ምንም የማይጨንቀው ሰው ነበር:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን በጾምና በጸሎት እየተጋ መምሕሩን ቅዱስ ዼጥሮስን ለመተካት [ለመምሰል] ይጥር ነበር::
ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምሕሩ ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል:: አርዮስ ክዶ: ቅዱስ ዼጥሮስ ካወገዘው በሁዋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን የአርዮስን ክፋት ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ዼጥሮስ ደቀ መዝሙሩን እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው::
"እኔ ከሞትኩ በሁዋላ አኪላስ ይተካል:: ከአርዮስ ጋር ስለሚወዳጅ በ፮ [6] ወሩ ይቀሠፋል:: አንተ ግን ከአርዮስ መርዝ ተጠበቅ" አለው:: ይህንን ካለው በሁዋላ ወታደሮች የቅዱስ ዼጥሮስን አንገት ቆረጡ:: ይህ የተደረገውም እ.ኤ.አ በ፫፻፲፩ [311] ዓ/ም ነው::
ወዲያውም አኪላስ ተሾመ:: እንደ ተባለውም ከአርዮስ ጋር ስለተወዳጀ በ፮ [6] ወሩ ተቀሰፈ:: በዚያው ዓመትም ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ [ግብጽ] ፲፱ [19]ኛ ፓትርያርክ [ሊቀ ዻዻሳት] ሆኖ ተሾመ::
ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ ተከታዮች ከተገመተው በላይ መበብዛታቸው ነው:: ቅዱሱ ሊቅ በዽዽስና መንበሩ ለ፲፯ [17] ዓመታት ሲቆይ ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም::
በዚህ እየጾመ: እየጸለየ: ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው ይገዛል:: በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል ያስተምራል:: ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ ለመታደግ ባፍም: በመጣፍም [በደብዳቤ] አስተማረ::
ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ አትናቴዎስ እያገዘው: አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት:: ለእያንዳንዷ የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ ባለፈ አርዮስን ከአንዴም ፪ : ፫ቴ [2: 3ቴ] በጉባኤ አውግዞታል::
ነገሩ ግን በዚህ መቁዋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ:: እ.ኤ.አ በ325 ዓ/ም [በእኛ በ፫፻፲፰ [318] ዓ/ም] ከመላው ዓለም ለጉዳዩ ፪ ሺህ ፫ መቶ ፵፰ [2,348] የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ:: ከእነዚህ መካከል ፫፻፲፰ [318]ቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ: ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ::
ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ እለአእስክንድሮስን መረጠ:: ሊቁም አበው ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን አርዮስን ተከራክሮ ረታው::
በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም" በማለቱ እርሱን አውግዘው: ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው: ፳ [20] ቀኖናወችን አውጥተው: መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው: አሥራው መጻሕፍትን ወስነው: ቤተ ክርስቲያንን በዓለት ላይ አጽንተው ተለያይተዋል:: የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ነው::
እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "ወልድ ዋሕድ: አምላክ: ወልደ አምላክ: የባሕርይ አምላክ" መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል:: የእምነታችንም መሠረቱ ይሔው ነው:: ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት ወምድር: የባሕርይ አምላክ: ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ [ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል]" ብለው ካላመኑ እንኩዋን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም::
ከጉባኤ ኒቅያ በሁዋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል: ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል:: ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን ምሰሶ ይወርድለት ነበር::
ስለ ውለታውም ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ ፭ [5]ቱ ከዋክብት ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች:: ቅዱሱ ሊቅ በ፫፻፳፰ [328] ዓ/ም [በእኛ በ፫፻፳ [320] ዓ/ም] በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::
ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቅልን:: ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን::
🕊
[ † ነሐሴ ፲፰ [ 18 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል [ ፫ኛ ቀን ]
፪. ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ
፫. ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን
፬. አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ [ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ ]
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
፪. አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት [ ረባን ]
፫. አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
፬. ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
፭. ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ [ከ፸፪ [72]ቱ አርድእት]
" . . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩአችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ::" [ይሁዳ.፩፥፫] (1:3)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖









