የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ወደ ዋና ዋና የኃይል ማመንጫ ግድቦች የሚገባው የውሃ መጠን ባለፉት ወራት በአማካይ 20 በመቶ ያህል መቀነሱን ገለጸ።
ተቋሙ ይህንን መረጃ በተከታታይ ክትትል ማረጋገጡን አስረድቷል።
የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ እንደገለጹት፣ ከሰኔ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ወደ ግድቦቹ የሚገባውን ውሃ ክትትል ሲደረግበት መቆየቱን ጠቁመው፣ ክትትሉም የተለያዩ የሜትሮሎጂ ትንበያዎችን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የኤልኒኖ ተጽዕኖው በዋናነት ያረፈው ከጠቅላላ የኃይል ምርት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በሚይዙት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ግቤ ሦስት ላይ ነው።
ከጠቅላላ የኃይል ምርት 65 በመቶ በላይ የሚሆነው ከእነዚህ ሁለት ግድቦች የሚገኝ ቢሆንም በክረምቱ ወቅት በታየው የዝናብ እጥረት "እነዚህ ሁለት ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የገባው የውሃ መጠን የ20 በመቶ ቅናሽ አለው" ሲሉ ዋና ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።
በእዚህም ምክንያት ምንም እንኳን ተቋሙ ለ 2019 ዓም የያዛቸው ዋና ዋና እቅዶች ከገቢ አንጻር ቅናሽ የታየባቸው ቢሆንም የማመንጨት አቅሙን በሚመለከት ግን ከ9,730 ሜጋ ዋት ወደ 9,770 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ አቅዷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2019 በጀት ዓመት ያወጣው እቅድ በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት ወደ ዋና ዋና ግድቦቹ በተለይም ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብና ግቤ ሦስት የሚገባው ውሃ በ20 በመቶ በመቀነሱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቅናሽ አሳይቷል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት 35,671 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ያመነጨ ሲሆን፣ ለ2019 ግን 32,134 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማምረት አቅዷል፤ ይህም ወደ 3,671 ጊጋ ዋት ሰዓት ወይም 10.3 በመቶ ቅናሽ ያሳያል።
በጠቅላላ ገቢ ረገድ፣ ተቋሙ በ2018 ከ124.2 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቶ የነበረ ሲሆን ለ2019 ዓም ደግሞ 121.2 ቢሊዮን ለመሰብሰብ አቅዷል፤ ልዩነቱም ወደ 3 ቢሊዮን ብር (2.4 በመቶ) ይደርሳል።
ተቋሙ በ2018 ከውጭ ምንዛሬ 475.7 ሚሊዮን ዶላር ያገኘ ሲሆን፣ ለ2019 ግን 278.63 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት በእቅድ ይዟል፤ ይህም ወደ 197 ሚሊዮን ዶላር ወይም 41.5 በመቶ ገደማ ቅናሽ ያሳያል።
ለዚህ ቅናሽ ዋነኛው ምክንያት ውሃ በመቀነሱ ለዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ይቀርብ የነበረው የኃይል መጠን ዝቅ እንዲል የሚደረግ በመሆኑ ነው።
የዝናቡን ውሃ እጥረት በሚመለከት ተቋሙ አሁን ላይ ሐምሌና ነሐሴ ወራትን ያለፈ ቢሆንም፣ ሙሉውን ምስል ለማየት መስከረምና ጥቅምት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጿል።
እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ ያለውን ትክክለኛ ሁኔታ ገምግሞ የዳታ ማይኒንግ አቅርቦትን መጨመር ወይም መቀነስ የሚቻልበትን ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስታውቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
#TikvahEthiopia
@Ethiopian_ICS0💌