በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ፣ በላቦራቶሪና በምርምር አቅም ጉልህ እድገት ማስመዝገቡን… — Ethiopian Public Health Institute | የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት — TG.ME

በድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ፣ በላቦራቶሪና በምርምር አቅም ጉልህ እድገት ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ገለጸ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው በጀት ዓመት በብሔራዊ የጤና ድንገተኛ ምላሽ፣ በዲጂታል የበሽታ ክትትል፣ በላቦራቶሪ ምርመራ እና በጥናትና ምርምር አቅም ማስፋፋት ጉልህ እድገት ማስመዝገቡን አስታወቀ።

ተቋሙ ይህን ያስታወቀው በዓመታዊ የግምገማ ስብሰባው ላይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ተቋሙ የሕብረተሰብ ጤናን ለማረጋገጥ የቅድመ-ማስጠንቀቂያና ዝግጁነት ሥራዎችን፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን አቅም ማጠናከርን እና የጤና ዲፕሎማሲን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የአደጋ ቅድመ-ማስጠንቀቂያና ዝግጁነት ሥራዎችም በአፋር፣ ሶማሌ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው፣ ኤምፖክስ፣ ኮሌራና ኩፍኝን ጨምሮ የተለያዩ የጤና ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱም፣ ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች የተመሠረተ ምላሽ መስጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የድንገተኛ አደጋ ቅንጅት ማዕከላት (EOCs) ከክልል ደረጃ ወደ ንዑስ ክልልና ዞን ደረጃ እየተስፋፉ መሆኑን ጠቁመዋል። በድንበር መግቢያና መውጫ ነጥቦችም ከ7.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዲጂታል የጤና ክትትል ምርመራ አግኝተዋል። በዲጂታል የበሽታ ክትትል በኩል፣ የDHIS2 ሽፋን ከ2024 ዓ.ም. 7 በመቶ ወደ 52 በመቶ አድጎ በአሁኑ ወቅት ከ81–85 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሮ አብደላ እንደገለጹት፣ የሪፈራል ላቦራቶሪ ምርመራዎች ከ113 ሺህ ወደ 217 ሺህ ናሙናዎች አድገዋል። ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪዎችን ወደ ወረርሽኝ ቦታዎች በመላክም ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ ሳያጓጉዙ በቦታው በ48 ሰዓታት ውስጥ ምርመራ ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል። የማርበርግ ቫይረስ በሽታ በተከሰተበት ወቅትም ተንቀሳቃሽ ላቦራቶሪ ወደ ጂንካ መላኩን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል።

የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርምር ሥራዎች ከመንግሥት ፖሊሲ፣ ከአገራዊ የጤና ቅድሚያዎችና ከሕብረተሰቡ የጤና ችግሮች ጋር እንዲጣጣሙ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። ተቋሙም ከክልል የምርምር ተቋማትና ከአካዳሚክ ማዕከላት ጋር የአቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የክልል ላቦራቶሪዎችንና የምርምር ተቋማትን አቅም ማጠናከር፣ ብሔራዊ ባዮባንክ ማቋቋም፣ የላቦራቶሪ ጥራት ማረጋገጫን ማጠናከር እና በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ጤና መካከል ያለውን የአንድ ጤና (One Health) ቅንጅት ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኃላፊዎችም በሰጡት አስተያየት፣ ኢንስቲትዩቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለው ለውጥ የሚበረታታ እና ፈለጉን ለመከተል ምሳሌ መሆን የሚችል እንደሆነ ገልጸዋል።
https://ephi.gov.et/ኢንስቲትዩቱ-በድንገተኛ-የሕብረተሰብ-ጤ/
https://x.com/EPHIEthiopia/status/2094763868891299929
https://www.facebook.com/share/p/19gxLHAaz5/
September 1, 2026 1.2K