የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2019 በጀት ዓመት የሥራ እቅድ ውይይት ተደረገበት::
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2019 በጀት ዓመት የሥራ እቅድና ዋና ዋና የአፈጻጸም አመልካቾችን ይፋ አደረገ፤ እቅዱ በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር፣ በላብራቶሪ አገልግሎት፣ በምርምርና በተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል በ215 ወረዳዎች የወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ዕቅዶችን ማጠናቀቅ፣ 14 ሀገራዊ የሙከራ ልምምዶችን ማካሄድ እና የጤና አደጋ ምላሽ አቅም ማሳደግን ያካትታል።
ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር፣ ዕቅዱ በቀረበበት ወቅትና የኢንስቲትዩቱ ዓመታዊ የግምገማ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢንስቲትዩቱ፣ የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች፣ ከክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የጋራ ቅንጅትና ጥረት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው በበጀት አመቱ የነበረውን አፈጻጸም በዝርዝር በመገምገሙ የነበሩ ጥንካሬዎችን ለማሳደግ እና ለ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ታቅደው ለተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎች በተሻለ ሁኔታ ለማዘጋጀት ማስቻሉን አብራርተዋል።
ዶ/ር መሳይ አያይዘውም በምርምርና መረጃ አያያዝ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን በማጠናከር፣ ሀገራዊ የህብረተሰብ ጤና ፖሊሲዎችንና ውሳኔዎችን በእውቀትና መረጃ ላይ የተመሰረቱ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የላብራቶሪ መሠረተ ልማቶችን ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 3 (BSL-3) እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን ማዘመን፣ ልኬቶችን ማስቀጠል እና የዲጂታል መረጃ ስርዓትን ማስፋፋት የሀገሪቱን የባዮ-ደህንነትና የመመርመር አቅም ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢንስቲትዩቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሕይወት አበበ እቅዱን ሲያቀርቡ፣ የተቀመጡት ግቦች ከሀገራዊ የጤና ዘርፍ ቅድሚያ ሰጪ ጉዳዮች፣ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እና አጋር ድርጅቶች የትግበራ ስትራቴጂዎች ጋር የተናበቡ እና የተጣጣሙ በመሆናቸው የጋራ የሥራ ማዕቀፍ በመሆን ያገለግላሉ ብለዋል።
ወ/ሮ ሕይወት ስለ ዕቅዱ ሲያብራሩ፣ በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ ዘርፍ፣ በ215 ወረዳዎች የወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ዕቅዶችን ማጠናቀቅ እና 14 ሙሉ ሀገራዊ የሙከራ ልምምዶችን ማካሄድ ታቅዷል። የPHEM-DHIS2 መረጃ ኤክስፖርት ትክክለኛነትና ሙሉነትን ወደ 85 በመቶ እና የትራከር ሪፖርት ሽፋንና ሙሉነትን ወደ 90 በመቶ ለማሳደግም ግብ ተይዟል።
የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ግምገማ ሪፖርቶችን በወቅቱ ሙሉ በሙሉ ማቅረብ እና ለሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የሚሰጠውን ምላሽ ከ80 ወደ 85 በመቶ ማሳደግ፣ በላብራቶሪ አገልግሎት ዘርፍ 250 ደረጃ በደረጃ ላብራቶሪዎችን ለማሻሻል ወደ እውቅና ለመሄድ የሚደረግ ልዩ ልዩ ስራዎችን ለመደገፍ፣ 80 ላብራቶሪዎችን ለISO 15189:2022 ዕውቅና ለማብቃት እና 2,500 የሕብረተሰብ ጤናና ክሊኒካል ላብራቶሪዎችን ካርታ ለማዘጋጀት መታቀዱን ዕቅዱ ያመላክታል።
በዕቅዱ በምርምር ዘርፍ 95 የምርምር ፕሮጀክቶች፣ 38 የቴክኒክ ምርምር ሪፖርቶች፣ 45 የማስረጃ አጫጭር መግለጫዎች እና 117 የበሽታዎች ጫና ግምገማ ሪፖርቶችን ለማጠናቀቅ፣ ሰባት የሀገር አቀፍ የፖሊሲ አጫጭር መግለጫዎችንም ለማተም፣ የምርምር ትኩረቶቹም የእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ የስነ-ተዋልዶ ጤና፣ ስነ ምግብ፣ ወባ እና ትኩረት የተነፈጋቸው የሐሩራማ በሽታዎች ተካተዋል።
የተቋሙን አቅም ለማጠናከርም 17,367 የጤና ባለሙያዎችን በአደጋ ቁጥጥር፣ በምርምርና በላብራቶሪ ዘርፎች ለማሰልጠን፣ 18 አዳዲስ የስልጠና ሞጁሎችን ለማዘጋጀት እና 18 አዳዲስ የስልጠና ፕሮግራሞችን ለመዘርጋት፣ ከአስራ አራት ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዷል።
ዶ/ር መሳይ የዓመታዊ የግምገማ ስብሰባውን የመዝጊያ ንግግር በማድረግ የሥራ መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ ተሳታፊዎች የኢንስቲትዩቱን የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማእከል፣ ቪ ኤች ኤፍ ላብራቶሪ (VHF Laboratory)፣ ጄኖሚክስ ላብራቶሪ (Genomics Laboratory) እና የስነ ምግብ ላብራቶሪዎችን በመጎብኘት ስብሰባው ተጠናቋል።
https://ephi.gov.et/የኢንስቲትዩቱ-የ2019-በጀት-ዓመት-የሥራ-እቅድ/
https://www.facebook.com/share/p/1HL1r1NDSz/
https://x.com/i/status/2095105686485024867
September 2, 2026 679