Dn Abel Kassahun Mekuria: post #1996 — TG.ME

+++ "ልጆቼ ከመሸ ተገናኘን" +++

ያኔ የገዳሙ መጋቢ የነበሩት አባ ተጠምቀ በጭንቀት ተውጠዋል። ከአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እግር ስር ወድቀው "ግድ የልዎትም አባ የዛሬው ጉዞ ይቆይዎ። እኔ ጥሩ ሕልም አላየሁም። እባክዎ እግርዎን ከዚህ ቤት አያንሡ፤ እንደው እባክዎ" እያሉ ይለምኗቸዋል። አቡነ ጎርጎርዮስ ግን ወደ መቂ ጊዮርጊስ ለአገልግሎት ለመሄድ ቆርጠው ተነሥተው ነበርና ሳልሄድ አላድርም ብለው እምቢ አሉ። በእርግጥ በዚያች የጉዞ ቀን ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀድመው ሳይረዱት ቀርተው አይመስልም። ምክንያቱም "ዛሬ ጥሩ ሕልም አላየሁምና አይሂዱ" ላሏቸው አባ ተጠምቀ " እኔስ ብሆን አንዳች ምልክት ያላየሁ ይመስልሃል። ዛሬ ጠዋት ሱሬን ስታጠቅ ሰባት ጊዜ መልሶ ሲፈታብኝ ነበር" ሲሉ መልሰውላቸዋል። ይሁን እንጂ በመቂ የሚገኝ እጅግ ሕመም የጸናበት አንድ የሚያውቁት ክርስቲያን ስለ ነበር ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ ለዚያ ሰው ነፍስ ዋጋ ሰጥተው "ኸረ ሳላቆርበው እንዳይሞትብኝ" እያሉ አባ ጎርጎርዮስ ወደ መኪናው ፈጥነው ወጡ። ነገር ግን ከዚያ መኪና በሕይወት አልወረዱም። ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጭኖ ከመጣ ተሽከርካሪ ጋር እርሳቸው ያሉበት መኪና ተጋጭቶ እሑድ ኃምሌ 22 ቀን ጠዋት አንድ ሰዓት ገደማ እኛ ደግ እና ባለ ብዙ ራእይ አባት አረፉ።

ብፁዕነታቸው ከማረፋቸው ከአንድ ሳምንት በፊት በአላጌ ሕፃናት አምባ የልጆች ማሳደጊያ ተገኝተው በዚያ ቦታ ለሚሠራ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ካኖሩ በኋላ "ሰው የሚፈልገውን ከሠራ የሚጠብቀው ሞቱን ነው" ብለው ተናግረው ነበር። በውስጣቸውም የነበረው የአገልግሎት እሳት ገና እየተቀጣጠለ ቢሆንም በዚህች ምድር የሚቀራቸው የእንግድነት ዘመን ግን ጥቂት መሆኑን ስለተረዱ በዚያ ለነበሩት መንፈሳዊ ልጆቻቸው እየደጋገሙ "ልጆቼ ከመሸ ተገናኘን" ይሏቸው ነበር። ከዚህች ክፋት ከነገሠባት ዓለም ጠልቀው ፈጣሪያቸው ካለበት መንፈሳዊ አገር የሚወጡበት ጊዜ መቃረቡን ቀድመው የተረዱ አባት ነበሩ።

አቡነ ጎርጎርዮስ ከዘመናቸው ቀድመው የኖሩ፣ ትውልዱ ሃይማኖቱን ያቆዩለትን አባቶች እንዲያውቅና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነቱንም ታሪክ ከመሠረቱ ተረድቶ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያፈቅር በቃልም በመጽሐፍም የተጉ አባት ናቸው። ቅዱስ አባታችን የነበሩበትን ዘመን አልፎ በሚሄደው ተራማጅ አሳቢነታቸውና ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ያሳዩት በነበረው ትጋት አሁን ላይ ላሉትና ወደ ፊትም ለሚነሡ በእውነት ለሚደክሙ ቅን አገልጋዮች ሁሉ ትልቅ አርአያ ይሆናሉ።

የአገልግሎት ድካማቸው በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን። እኛንም የአባቶቻችን ልጆች ያድርገን!!!

(*የያኔው አባ ተጠምቀ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳይ የምሥራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው።)

ዲያቆን አቤል ካሣሁን
ሐምሌ 22፣ 2014 ዓ.ም.
(የብፁዕነታቸው የዕረፍት ቀን)

ዝዋይ (ብፁዕነታቸው ብዙ ሥራ በሠሩበት ክፍለ አገር ሆኜ)
❤168🙏36👍6🤔1
July 29, 2026 7.6K 4 36