በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 2,500 ዘመናዊ ቤቶች ይገነባሉ፡፡ አዲስ አበባ | ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 2,500 የመኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ። የክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ አካል የሆነውን ይህንን የቤት ግንባታ ፕሮጀክት፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአራዳ ክፍለ ከተማ 8 ባለ ዘጠኝ ወለል ህንፃዎችን ያካተተ "የበጎነት መንደር" ግንባታን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል። በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ "የመረጠንን ህዝብ የምናመሰግነው በቃላት ሳይሆን በተግባራዊ ምላሽ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ዳግም ኢትዮጵያን ለመምራት ተጨማሪ የአምስት ዓመት እምነት በተሰጠው ማግስት የተጀመረ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ከዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃዎች በተጨማሪ ባለ 4 ወለል ሁለት የገበያ ማዕከላትን ያካተተ ነው። የበጎነት መንደሩ ለዘመናት የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በመቀየር ለሰው ልጆች ክብር የሚመጥን ዘመናዊ የጋራ መገልገያዎችን፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን እና የስፖርት ሜዳዎችን ያካተተ ይሆናል። የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በ16 ዓበይት ፕሮግራሞችና በ19 ንዑስ መርሃ ግብሮች የሚተገበር ሲሆን፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 5,846 ቤቶችን በመገንባት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ 38,898 ነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል። የዘንድሮው የክረምት የቤት ግንባታ መርሃ ግብር ከሌላው ጊዜ የሚለየው፣ የሚገነቡት 2,500 ቤቶች በሙሉ ከሁለት ወለል በላይ መሆናቸው ነው።
የኀብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - አዲስ አበባ: post #2481 — TG.ME
June 22, 2026 245