AARB Arada Branch Customer service: post #187 — TG.ME

Forwarded fromTITIKVAH-ETHIOPIA

በአዲስ አበባ ከተማ በሆቴሎች እና ተመሳሳይ ተቋማት የመኝታ አገልግሎት ላይ የ5 በመቶ ማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ ተጣለ። ⚫️ በአዲሱ ደንብ ድንጋጌ መሰረት ማንኛውም የመኝታ አገልግሎት ሰጪ ተቋም የመኝታ ክፍሎቹን ብዛትና የእያንዳንዱን ክፍል የቀን የዋጋ ዝርዝር በገቢዎች ቢሮ በአካል ቀርቦ በልዩ ቅጽ መሙላትና ማሳወቅ ይኖርበታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሆቴሎች፣ በሪዞርቶች፣ በሞቴሎች እና በሌሎች መሰል የመኝታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ አዲስ የማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ የሚጥል ደንብ አወጣ። "የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመኝታ አገልግሎት ማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ ደንብ ቁጥር 204/2018" በሚል የወጣው ይህ ደንብ፣ የከተማዋን የገቢ አቅም ለማሳደግና መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። በደንቡ አንቀጽ 6 መሠረት፣ ማንኛውም የመኝታ አገልግሎት ተጠቃሚ ለክፍል አገልግሎት ከሚከፍለው ዋጋ ላይ 5 በመቶ (5%) የማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ እንዲከፍል ይደረጋል። ይህ የታክስ ተመን የሚሰላው የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ሳይታከልበት ባለው መደበኛ የክፍል ዋጋ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ተደንግጓል። ይህ አዲስ የታክስ ሕግ በከተማዋ አስተዳደር ወሰን ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የመኝታ አገልግሎት ሰጪዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ እነዚህም፦ • ከ1 እስከ 7 ኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እና ኮከብ የሌላቸው ሆቴሎች፣ • ሪዞርቶች፣ ሎጆች እና ሞቴሎች፣ • የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች (Guest Houses) እና ፔንሲዮኖችን ያጠቃልላል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ በየወሩ ወይም በየሦስት ወሩ (እንደ ግብር ከፋይ ደረጃቸው) የሰበሰቡትን ታክስ ለከተማው ገቢዎች ቢሮ ሪፖርት የማድረግና ገቢ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል። ደረጃ "ሀ" ግብር ከፋዮች  በየወሩ ሪፖርት አድርገው ገቢ የሚያደርጉ ሲሆን ደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች ደግሞ በየሦስት ወሩ ሪፖርት አድርገው ገቢ ያደርጋሉ። ደንቡን በማይተገብሩ፣ ሪፖርት በሚያዘገዩ ወይም የገቢ መረጃ በሚደብቁ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ቅጣት እንደሚጣል ተመልክቷል። ለማሳያም ሪፖርት ያዘገየ ተቋም ካለበት ዕዳ ላይ እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችልና የታክስ መረጃ መደበቅ ደግሞ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ተደንግጓል። እንደ ደንቡ ድንጋጌ፣ ማንኛውም የመኝታ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በገቢዎች ቢሮ በአካል ቀርቦ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በሚመዘገብበት ወቅትም የተቋሙን የክፍሎች ብዛትና የእያንዳንዱን ክፍል የቀን የዋጋ ዝርዝር በልዩ ቅጽ መሙላትና ማሳወቅ ይኖርበታል። ይህ የታክስ አከፋፈል ሂደት ከተቋማቱ የንግድ ፈቃድ እድሳት ጋርም በቀጥታ የተያያዘ ነው። የከተማዋ የቱሪዝም ኮሚሽን የሆቴሎችን የሙያ ብቃት ፈቃድ የሚያድሰው ተቋማቱ ታክሱን በአግባቡ መክፈላቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ ደብዳቤ ከገቢዎች ቢሮ ሲያቀርቡ ብቻ መሆኑ በደንቡ ላይ በግልጽ ተቀምጧል። የታክስ አሰባሰቡን ግልጽነት ለማረጋገጥም፣ ተቋማቱ በሚሰጡት የሽያጭ ደረሰኝ ላይ "የማዘጋጃ ቤታዊ መኝታ አገልግሎት ታክስ" የሚለው ሐረግ በግልጽ እንዲሰፍር ታዟል። የሒሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የሌለባቸው ግብር የሚከፍሉ ተቋማት ደግሞ ከሚሰጡት አገልግሎት 70 በመቶው ላይ የ5 በመቶ ታክስ ታስቦ እንዲከፍሉ ይደረጋል። በተጨማሪም ተቋማቱ የሰበሰቡትን የታክስ ገቢ በየወሩ ጠቅልለው ሪፖርት ከማድረጋቸው ባለፈ፣ ሰብስበው ባጠናቀቁ በ30 ቀናት ውስጥ ለዚሁ ተብሎ ወደተከፈተ የባንክ ሒሳብ ገቢ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም በታክስ አሰባሰብና በአሠራር ሂደት ላይ ቅሬታ ካላቸው በየደረጃው ለሚገኝ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የማቅረብ መብት አላቸው። ኮሚቴው ቅሬታውን ተቀብሎ በ15 የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት ያለበት ሲሆን፣ በውሳኔው ቅር የተሰኘ ወገን ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ለከተማ አስተዳደሩ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል። ማንኛውም የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከመኝታ አገልግሎት የተገኘን ገቢ ወቅቱን ጠብቆ ሪፖርት አለማሳወቅ ለዘገየበት በየወሩ 5 ከመቶ ከክፍያው ከ50 ከመቶ ያልበለጠ ቅጣት እንዲከፍል ይደረጋል። በተጨማሪም የታክስ ገቢውን በወቅቱ ገቢ ያላደረገ ተቋም በወቅታዊ የባንክ ብድር ወለድ ተመን መሠረት ወለድና በወለዱ ላይ ተጨማሪ 15 በመቶ ቅጣት እንዲከፍል ይደረጋል። አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነቷ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለከተማዋ የልማት ስራዎች ለማዋል ታስቦ የወጣ መሆኑን የመግቢያው ክፍል ያስረዳል። ይህም የከተማዋን የገቢ መሠረት በማስፋት የንግድ እንቅስቃሴው ለከተማዋ እድገት የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ያደርጋል ተብሏል። ይህ ደንብ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተፈርሞ የወጣ ሲሆን፣ ከሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ሆኗል። ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሃምሌ 3 ቀን 2018 ዓ/ም @tikvahethiopia

July 10, 2026 1.4K 7