አዲስ አበባ የአየር ንብረት አደጋዎችን በመቋቋም በዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ ታሪካዊ የምሥራች አበሰረች ዓለም… — Addis Ababa Health Bureau / አዲስ አበባ ጤና ቢሮ / AACAHB / — TG.ME

አዲስ አበባ የአየር ንብረት አደጋዎችን በመቋቋም በዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ ታሪካዊ የምሥራች አበሰረች

ዓለም አቀፉ የጂኦስፓሻል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም አልፋጂኦ (AlphaGeo) የዓለም ታላላቅ 72 ከተሞችን የአየር ንብረት አደጋ የመቋቋም አቅም (Climate Resilience) አመላካች ይፋ አድርጓል።

በዚህ አዲሱ ዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት መዲናችን አዲስ አበባ ከዓለም አቀፍ ከተሞች ሁሉ በ2ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ አስደናቂ ስኬት አስመዝግባለች።

ጥናቱ የከተሞችን ዝግጁነት የለካው ከተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭነት ነጻ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን አደጋዎችን የመከላከል፣ የማላመድ እና የመቋቋም አቅማቸውን መሠረት በማድረግ ነው።

በዚህ መሠረት የአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ በ1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ አዲስ አበባ ደግሞ እንደ ሜልቦርን፣ ባርሴሎና እና ፓሪስ ያሉ ታላላቅ የዓለም ከተሞችን በልጣ በዓለም 2ኛ ተስፋ ሰጪ እና ጽኑዕ ከተማ በመሆን ተመዝግባለች።

ይህ ታሪካዊ ውጤት በአዲስ አበባ ከተማ በመከናወን ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፣ የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ለከተማዋ አደጋዎችን የመቋቋም አቅም ያበረከቱትን ታላቅ አስተዋጽኦ በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ጥናቱ እንደሚያመላክተው፣ ብዙኃኑ የደቡብ እስያ ከተሞች ለአየር ንብረት አደጋ ከፍተኛ ተጋላጭ ሆነው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ወድቀዋል።

በዚህ ወቅት ታዲያ አዲስ አበባ ያስመዘገበችው ይህ የላቀ ደረጃ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ የከተሞች ልማት ላይ የምታደርገው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ነው።

መዲናችን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ደኅንነቷ የተጠበቀ የጽናት ተምሳሌት መሆኗን እየኖሩባት ላሉት ሁሉ የየቀን እውነት ቢሆንም አሁን ደግሞ ለዓለም ሁሉ የታወጀ ታላቅ ብስራት ነው።
September 8, 2026 564