ቻይና ቁመቱ 7 ሜትር የሆነ ግዙፍ የሮናልዶ ሀውልት አቆመች!
በመላው ዓለም የሚገኙ አድናቂዎቹ ለክርስቲያኖ ሮናልዶ ያላቸውን ክብር በተለያየ መንገድ መግለጻቸውን ቀጥለዋል፤ አሁን ደግሞ በቻይና ሻንጋይ ከተማ ቁመቱ 7 ሜትር የሆነ ግዙፍ የሮናልዶ ሀውልት ተመርቋል። ታዋቂውን የፖርቹጋል 7 ቁጥር ማሊያ ለብሶ ዝነኛውን "ሱ..ሱ…ሱ" (Siuuu) የደስታ አገላለጽ እያሳየ የተሰራው ይህ ሀውልት፣ በሻንጋይ 'ኢስት ናንጂንግ' መንገድ ላይ ከአዲሱ 'ሲአር7' (CR7) ሙዚየም ፊት ለፊት ቆሟል።
በምርቃቱ ወቅት ሮናልዶ ባይገኝም ታላቅ ወንድሙ ሁጎ አቬሮ እና የቅርብ ጓደኛው ሚጌል ፓይክሳኦ የተገኙ ሲሆን፣ የሀውልቱ መጋረጃ ሲገለጥ በስፍራው የነበሩት በርካታ አድናቂዎች በአንድ ድምፅ "ሱ..ሱ…ሱ" ብለው ሲጮሁ ስፍራውን አድምቀውታል።
ከሀውልቱ ምርቃት ጋር ተያይዞ የተከፈተው እና 3,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የ'ሲአር7' ሙዚየም፣ 10 ዋና ዋና ክፍሎችና ከ40 በላይ መታሰቢያ ዕቃዎችን አካትቷል። በሙዚየሙ ውስጥ የተጫዋቹ ዋንጫዎች፣ ማሊያዎችና ጫማዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይም ሮናልዶ ልጅነቱን ያሳለፈበትን በማዴይራ የሚገኘውን መኝታ ቤቱን አስመስሎ የተሰራው ክፍል የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። የቻይና ሚዲያዎች እንደዘገቡት ሙዚየሙ ለአንድ ዓመት ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ ግዙፉ ሀውልት ግን ለአንድ ወር ያህል ማለትም እስከ ታኅሣሥ (ዲሴምበር) 2026 ድረስ በስፍራው ይቆያል።

November 23, 2026 179