ምንፍቅና ነው !
“ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እርሱ ለሦስት ቀን እና ለሦስት ሌሊት በሞተ ጊዜ ዓለምን ሲቆጣጠር የነበረው ማን ነው ?” ለሚለው የተለመደ የሙስሊሞች ጥያቄ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምላሽ ሲሰጡ ጥያቄው እንደ መቅድመ ልባዌ (Presupposition) የያዘው የሞት ትርጉም ላይ በመንተራስ “አርጕዌንዶ” [1] ይሞግታሉ። ይኸውም የተንባላት ሙግት ሞት ማለት የህልውና መጥፋት ወይንም መኖር ማቆም ነው የሚል እሳቤ ላይ እንደተመሰረተ በማመልከት ፣ በዚህ የሞት ትርጉም መሰረት ብንሄድ እንኳ ወልድ ሲሞት አብ እና መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸውና እነርሱ ዓለምን ይቆጣጠራሉ የሚል ነው። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ምላሽ በኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሥላሴ ላይ ተፋልሶ የሚያመጣ አልፎ ተርፎም ወደ መድብለ አማልክታዊነት የሚከት ስሁት ምላሽ ነው። ስለ ሁለት ምክንያቶች :-
1). የባሕርይ መገናዘብን ይክዳል።
እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከሆነ በሥላሴ አካላት መካከል በፍጥረት ዘንድ የሌለ የባሕርይ መገናዘብ ያለ ሲሆን ይህም አብ በወልድ ፣ ወልድ በአብ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ በአብ እና በወልድ ህልው መሆን ነው። ስለሆነም በባሕርይ ተመሳሳይ በሆኑ ፍጥረታት ዘንድ የምናስተውለው የአንዱ አለመኖር የሌላኛውን ህልውና አለመንካት በሥላሴ አካላት ዘንድ የለም ፤ በዚህም መለኮት ኢ-መዋቲ ነው እንጂ ከሥላሴ አካላት አንዱ በመለኮት ቢሞት ኖሮ (መኖር ቢያቆም) ሌሎችም አካላት ይሞታሉ። ከዚህ የተለየ እሳቤ ያለው ሰው ካለ ፣ የሥላሴን አካላት እንደ አንድ አምላክ ሳይሆን እንደ ሦስት አማልክት ወደ ማየት ተሻግሯል ማለት ነው። ይህን እውነት ሊቀ-ሊቃውንት ስምዐኮነ በዚህ መልኩ ፍንትው እና ቁልጭ አድርገው ገልጸውታል :-
«የእኛን ልደት ስናይ ግን የአካልም የባሕርይም አንድነት እንዳይኖረን የሚያደርግ ፍጻሜ ፣ ማኅለቅት ያለው ልደት ስለምንወለድ በህልውና አንገናዘብም። በባሕርይ ብንመሳሰል እንጂ በባሕርይ በህልውና አንድ አንሆንም። ስለዚህም አንዱ ሲሞት ሌላው አይሞትም። በሥላሴ ባሕርይ ግን አንዱ የሚሞት ቢሆን ኖሮ ሌላውም ሕያው ባልሆነ ነበር ...» [2]
2). የአፍአዊ ግብር አንድነትን ይክዳል።
አፍአዊ ግብር በኦርቶዶክሳዊ ነገረ ሥላሴ ውስጥ ሦስቱ የሥላሴ አካላት ከፍጥረት ጋር በተያያዘ የሚሰሩትን ማንኛውንም ግብር የሚያመለከት ሲሆን በባሕርይ አንድ የሆኑ አንድ አምላክ እንደ መሆናቸው ይህ ግብር በአካላት ልክ ተፈልጦ የሌለበት በቁጥር አንድ (numerically identical) ነው።[3] ይህ በቁጥር አንድ የሆነ አፍአዊ ግብር እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ያሉ አባቶች ቅድስት ሥላሴ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት ሊባሉ እንደማይገባ የሚያቀርቡት ሙግት አስኳል ነው። ስለሆነም አብ እና መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ተለይተው የሚሰሩት ምንም ዓይነት ሥራ እንደሌለ እየታመነ ፣ ወልድ ቢሞት አብ እና መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ይጠብቃሉ ማለት የአፍአዊ ግብር አንድነትን መካድ ነው።
አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና !
✍ ዲ/ን ዘአትናቴዎስ
🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱🌱
1). አርጕዌንዶ (Arguendo) የላቲን ቃል ሲሆን ትርጉሙ ለሙግት ሲባል (for the sake of argument) ነው፤ ይህም በህግ ክርክር እና በአመክንዮ ውስጥ አንድን ሃሳብ ለሙግት ሲባል እንደ መቅድመ ልባዌ ይዞ መነሳትን ለማመልከት የሚውል ነው።
2). ተንከተም በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ፣ ገጽ.167-168
3). «... the doctrine of inseparable operations ad extra ... This doctrine says that all the activities of the three hypostases of the Trinity, at least insofar as they relate to things outside of (“ad extra”) the Trinity (i.e., as they relate to all created beings) are not only qualitatively identical or identical in kind, but numerically identical--that is, they perform literally the same particular (token) actions--and thus are united in their activities in a way that men, angels and other created beings cannot be.» [Gregory of Nyssa on the Individuation of Actions and Events by Beau Branson]