ያሬድ ዘርአ-ቡሩክ ▪️መጋቤ ምስጢር: post #2500 — TG.ME

በሥላሴ መካከል የሥልጣን መበላለጥ የለም። ቅዱስ ሳዊሮስም “ወአልቦ በውስተ ቅድስት ሥላሴ ግብርናት ወኢ ተጋንዮ ወኢይትሌዐል አሓዱ እምካልኡ በመዓርገ መለኮት ወኢይኤዝዞ አሓዱ ለካልኡ ዘከመ ተለኣኪ በሥልጣኑ አላ እሙንቱ ዕሩያን በአሓዱ ክብር ዘመለኮት ወምልክና ወሉዓሌ ብርሃን ዘአኃዜ ኵሉ - በሦስቱ አካላት ውስጥ መገዛት፣ መታጠቅና መፍታት የለም፤ በመዓርገ መለኮትም አንዱ ካንዱ አይበልጥም፤ አንዱ አንዱን እንደ መልእክተኛ አድርጎ በሥልጣኑ አያዝዘውም፤ በአንድ መለኮት ክብርና በአገዛዝ የሁሉ ፈጣሪ ገንዘብ በሚሆን በባሕርይ ዕውቀት አንድ ናቸው እንጂ።” ብሏል። ሃይ. አበ. ፹፬፡፮።

         ሥላሴ አምላክ ወይስ አማልክት?

           ሥላሴ አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም። ቅዱስ አትናቴዎስም “አምላክ ውእቱ አብ፥ ወአምላክ ውእቱ ወልድ፥ ወአምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ ወኢይትበሀሉ ሠለስተ አማልክተ አላ አሓዱ አምላክ - አብ አምላክ ነው፤ ወልድም አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፤ ነገር ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም።” ብሏል። ሃይ. አበ. ፳፭፡፬።

ቅዱስ ጎርጎርዮስም “ወኢንሰግድ ለሠለስቱ አማልክት አላ ለአሓዱ አምላክ - ለአንድ አምላክ እንሰግዳለን እንጂ ለሦስት አማልክት አንሰግድም።” ብሏል። ሃይ. አበ. ፷፡፮።

         ቅድመ ዓለም የወልድ ከአብ መወለድ አይመረመርም። ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ሳያንስና ሳይበልጥ አብን አህሎ፥ አብን መስሎ ከአብ አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ ተወልዷል። አብ ወልድን ከባህርዩ የወለደበት ዘመንም አይታወቅም። ጥንትም የለውም። የወለደበት ምስጢርም በመላእክትም ሆነ በሰዎችም አእምሮ አይታወቅም።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘቂሳርያም “ወልደቱሰ ለወልድ እምአብ ዘኢይትረከብ ወኢይትከሀል ተናግሮቱ እስመ መንፈሳዊ ውእቱ እንበለ ተኃሥሦ እስመ ለመንፈሳዊ ኢይክል ሥጋዊ ረኪቦቶ ወኢይደልዎ ይትኃሠሥ በእንቲኣሁ እስመ ኢይትማሰል በህላዌ እጓለእመሕያው ወኢኮነ ልደቱ ከመ ልደተ እጓለእመሕያው ዐቢይ ምስጢር ውእቱ ወኢይትረከብ - የወልድ ከአብ መወለዱ የማይመረመር ሊናገሩትም የማይቻል ነው፤ የማይመረመር ረቂቅ ስለሆነ ግዙፉ ረቂቁን መርምሮ ማወቅ የማይቻለው ነውና፥ የርሱን ነገር ይመረምር ዘንድ አይቻለውምና፥ ከሰው ባሕርይ ጋርም አይመሳሰልምና፥ ልደቱም እንደ ሰው ልደት አይደለምና ረቂቅ ምስጢር ነው። አይመረመርም።” ብሏል። ሃይ. አበ. ፲፫፡፲፩-፲፪።

             ከአብ ወልድ ሳይወለድና መንፈስ ቅዱስ ሳይሠርጽ የተቈጠረ ጊዜ የለም። “ወልድ ከአብ በተወለደበት ቅጽበት መንፈስቅዱስ ከአብ ሳያንስና ሳይበልጥ አብን አህሎ፥ መስሎ አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ ከአብ ሠርጿል። ወይም መንፈስ ቅዱስ ከአብ በሠረጸበት ቅጽበት ወልድ ከአብ ተወልዷል። በወልድ ከአብ መወለድና በመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ መካከል መቅደም መቀዳደም የለም። አብም ወልድን ቢወልድና መንፈስቅዱስን ቢያሠርጽም ከወልድና ከመንፈስቅዱስ በዘመን አይቀድምም፤ በሥልጣንም አይበልጥም። አብ መንፈስቅዱስን ያሠረጸበት ዘመንም ከቶ አይታወቅም። ጥንትም የለውም። ከባህርዩ ያሠረጸበት/ያስገኘበት ምስጢርም በመላእክትም ሆነ በሰዎች አእምሮ አይታወቅም።

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም “ኢነአምር ዘከመ እፎ ወለዶ አብ ለወልድ ወዘከመ አሥረጾ ለመንፈስ ቅዱስ - አብ ወልድን እንዴት እንደ ወለደውና መንፈስቅዱስን እንዴት እንዳሠረጸው አናውቅም።” ብሏል።” መጽ. ምስ. ፫፡፲፰።

ቅዱስ ዲዮናስዮስም “ልደተ ወልድ ወፀአተ መንፈስ ቅዱስ እምአብ ይትነከር ወኢይትነገር ወይትሌዐል ላዕለ ኵሉ ሕሊናት ወኢይትረከብ - ከአብ የወልድ መወለድና የመንፈስ ቅዱስ መሥረጽ በዕፁብ ይወሰናል እንጂ እንዲህ ነው ተብሎ አይነገርም፤ ከሕሊናት ሁሉ በላይ ነው፤ አይመረመርም።” ብሏል። ሃይ. አበ. ፲፡፲፩።

       #ማስታወሻ፦
የሥላሴ የአካል፣ የግብርና የባሕርይ ከዊን ስሞች፦
• በአካል የሚጠሩባቸው ስሞች፦ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፤
• በግብር የሚጠሩባቸውን ስሞች፦ ወላዲ/አሥራጺ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ፤
• በባሕርይ ከዊን የሚጠሩባቸው ስሞች፦ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ፤

ጦማሪ፦ መጋቤ ምስጢር ያሬድ ዘርአ-ቡሩክ
July 14, 2026 901 1 3