በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በሚሽነሪዎች ዓለም ከተፈጠሩት እጅግ አወዛጋቢና የረቀቁ ስትራቴጂዎች አንዱ "የውስጥ እንቅስቃሴ" (The Insider Movement - IM) የተሰኘው ስልት ነው። የዚህ ስልት ዋነኛ ፍልስፍና "አንድ ሙስሊም ክርስቲያን ለመሆን ዲናዊ የነበረውን አኗኗሩን፣ ማህበረሰቡንና ሃይማኖታዊ መለያውን መተው የለበትም" የሚል ነው።
ከዚህ ቀደም ሰዎች እምነታቸውን ሲቀይሩ ስማቸውን ለአብነት ከ'መሀመድ' ወደ 'ጳውሎስ' ይቀይራሉ፣ ከመስጊድ ወጥተው ወደ ቤተክርስቲያን ይሄዳሉ። ይህ ግን በማህበረሰቡ ዘንድ መነጠልንና ከፍተኛ ተቃውሞን ስለፈጠረባቸው፣ አዲሱ ስልት ሰውዬው ራሱን "ሙስሊም" ብሎ እየጠራ፣ ነገር ግን በውስጡ የክርስትናን ዶክትሪን ተሸክሞ በማህበረሰቡ ውስጥ "የውስጥ አርበኛ" ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ የረቀቀ የስነ-ልቦና ስልት ነው።
ይህ ስልት መሬት ላይ እንዴት እንደሚተገበር የሚያሳየውን የመጀመሪያውን ተጨባጭ ምሳሌ እንመልከት፦ "የኢሳ ተከታይ ሙስሊሞች" (Messianic Muslims) የሚባለው አደረጃጀት ነው። በእነዚህ ሚሽነሪዎች የተጠመቀ አንድ ሙስሊም፣ የሙስሊም ስሙን አይቀይርም፣ የቀድሞ አለባበሱን አይተውም፣ አልፎ ተርፎም በቀን አምስት ጊዜ ወደ መስጂድ መሄዱን እና በረመዳን መጾሙን ሁሉ እንዲቀጥል ይደረጋል። ሆኖም መስጂድ ውስጥ ግንባሩን መሬት ላይ አስደግፎ ሱጁድ ሲያደርግ፣ ዱዓውን የሚያደርገው በአዲሱ ሚስጥራዊ እምነቱ መሠረት ለ"ጌታ ዒሳ" (ኢየሱስ) ነው። ሲጠየቅም "እኔ ክርስቲያን አይደለሁም፤ እኔ ዒሳ አል-መሲህን የምከተል ሙስሊም ነኝ" ይላል።
ጆን ትራቪስ የተባለው ታዋቂው ሚሽነሪ ባዘጋጀው የስልት መለኪያ (C1-C6 Spectrum) መሠረት፣ ይህ 'C5' የተባለው ከፍተኛው የስውርነት ደረጃ ሲሆን፣ ማህበረሰቡ ሰውዬውን እንደ አንድ ጽኑ ሙስሊም ሲያየው፣ እሱ ግን በውስጡ የክርስትናን አስኳል ተሸክሞ ሌሎችን በድብቅ ይመለምላል።
ሁለተኛውና እጅግ አስደንጋጩ ምሳሌ ደግሞ በአንዳንድ የእስያና የአፍሪካ ሀገራት የተሞከሩት "መስጊድ-መሰል ማምለኪያ ስፍራዎች" (Contextualized Worship Spaces) ናቸው። በዚህ ስልት መሰረት፣ ሚሽነሪዎቹ የሚተክሉት ቤተክርስቲያን ከውጭ ሲታይ መስቀል የሌለውና ልክ እንደ መስጂድ የተቀረጸ ነው። ውስጥ ሲገባ ምንጣፍ ተነጥፏል፤ ተሳታፊዎቹ ጫማቸውን አውልቀው፣ ወንዶችና ሴቶች ተለያይተው ይቀመጣሉ። አምልኮው የሚመራው "ፓስተር" በማይባል ነገር ግን "ሸይኽ" ወይም "ኢማም" በሚባል መሪ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡት ልክ ቁርዓን እንደሚቀራው በሚስብ የ"ቲላዋ" አይነት ዜማ ነው።
መዝሙራቸውም በአካባቢው በሚታወቁ ኢስላማዊ የቃላት አወቃቀር ያለው የዚክር ዓይነት ነው። አንድ ተራ ሙስሊም አጋጣሚ በሩን ከፍቶ ቢገባ መስጊድ ውስጥ ያለ እንጂ ቤተክርስቲያን የገባ አይመስለውም። ይህ የሃይማኖቶች ድንበር ሙሉ በሙሉ የፈረሰበት ስልት፣ እስልምናን በራሱ መለያዎች በመጠቀም ከውስጥ ለመቦርቦር የተነደፈ ነው።
የዚህ "የውስጥ እንቅስቃሴ" ታላቁ አደጋ ማህበረሰቡን ስነ-ልቦናዊ ግራ መጋባት ውስጥ መክተቱ ነው። ማህበረሰቡ 'ይህ የኛ ነው ወይስ የነሱ?' የሚለውን መለየት እስኪያቅተው ድረስ ድንበሩ ይደበዝዛል። ሚሽነሪዎቹ የሰውን ልጅ መንፈሳዊ ማንነት ልክ እንደ ኮምፒውተር ሶፍትዌር ሃርድዌሩን (የውጪውን ሙስሊም ገጽታ) ሳያስነኩ፣ ሶፍትዌሩን (የውስጡን እምነት) በመቀየር ማህበረሰቡ የራሱን በሽታ መከላከል እንዳይችል ያደርጉታል።
ረቢካ ሉዊስ የተባለችው የሚሽነሪ ስትራቴጂስት እንደጻፈችው፣ "ግቡ ሰዎችን ከእስልምና ማውጣት ሳይሆን፣ እስልምናን በክርስቶስ ማጥለቅለቅ ነው" ትላለች። ይህ እጅግ የተራቀቀ የማንነት ጠለፋ፣ ትውልድን ያለ ጦርነት የማተራመስ አላማ በጸጥታ ያነገበ የትሮጃን ፈረስ ነው።
የመረጃ ምንጮች፦
- Rebecca Lewis, "Promoting Movements to Christ within Natural Communities".
- John Travis, "The C1 to C6 Spectrum: A Practical Tool for Defining Six Types of Christ-Centered Communities Found in the Muslim Context".
በቀጣዩ ክፍል በአላህ ፍቃድ የምንዳስሰው አጀንዳ፦
የወጣቱን አእምሮ መቆጣጠር እንዲቻል የተነደፈውን የዘመናዊ ትምህርት ስልትና ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ምልመላ ማዕከል የመጠቀምን ስትራቴጂን (Campus Crusades and Education) በቀጣይ ክፍል - 17 በአላህ ፍቃድ እንመለከተዋለን።
ያለፉትን ክፍሎች ለማንበብ
ፌስቡክ | ዋትስአፕ
76
18
4
3August 25, 2026 4.4K 15