በቅርቡ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር ላይ ሲውል የነበረውን እና ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለውን… — የሕያ ኢብኑ ኑህ | Yahya Ibnu Nuhe — TG.ME

የሕያ ኢብኑ ኑህ | Yahya Ibnu NuhePhoto
በቅርቡ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር ላይ ሲውል የነበረውን እና ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለውን "ዓ.ም." (ዓመተ ምህረት) በመተው፣ ሁሉንም አቃፊና ገለልተኛ እንደሚሆን በተስማሙበት "ዓ.ል." (ዓመተ ልደት) ወይም "እ.ኢ.አ." (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) እንሸጋገር የሚል ሀሳብ አቅርቧል። ይህን ተከትሎ ግን በአንዳንድ የኦርቶዶክስ እምነት አክቲቪስቶች ዘንድ ሰማይ ምድሩን የሚያቀልጥ ጩኸት እየሰማን ነው። አንዳንዶችም "ለምን የኛን ተውት ትላላችሁ? ሂጅራስ ለምን ሆነ?" እያሉ እያማረሩ ነው።

​እዚህ ላይ ግን በግልጽ መነጋገር ያለብን እጅግ አስገራሚ ደብል ስታንደርድ አለ። ​በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሙስሊሙ የራሱ የሆነ የ"ሂጅራ" ዘመን አቆጣጠር አለው። ሂጅራ የሚያመለክተው የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ከጥቃት ለመሸሽ ያደረጉትን ታሪካዊ ስደት እንጂ፣ በማንም እምነት ላይ ጣልቃ የሚገባ (ቲዮሎጂያዊ) ትርክት የለውም።

ይህን የሂጅራ አቆጣጠር "የኛን አይወክልም" በማለት እንዳንጠቀምበት ሲያወግዙ የነበሩ ወገኖች፣ ዛሬ ላይ ደግሞ ተመልሰው "ሙስሊሙን ጨምሮ ሁሉም ሰው 'ዓመተ ምህረት' ብሎ ካልጠራ ሞቼ እገኛለሁ" ማለታቸው የግብዝነት ጥግ ነው። የራስህን ሃይማኖታዊ መለኪያ በሌላው ላይ መጫን መብት አይደለም! ፈልገህ "ዓ.ም" ብለህ መጠቀም መብትህ እንደሆነው ሁሉ፣ የሌላውን አለመጠቀምም ማክበር ግዴታህ ነው።

​እኛ ሙስሊሞች "ዓ.ም" (ዓመተ ምህረት) የሚለውን ለምን አንቀበለውም?

ይህ ጉዳይ ከእልህ ወይም ከፖለቲካ ሳይሆን፣ ቀጥታ ከእስልምና ዐቂዳ ጋር የሚያያዝ ነው። እስልምና የነብዩላህ ዒሳን ድንቅ አፈጣጠር ይቀበላል። ነገር ግን "ዓመተ ምህረት" ሲባል ከጀርባው ያለው ሃይማኖታዊ እሳቤ በእስልምና ፍጹም ተቀባይነት የለውም። ለምን የሚለውን በአጭሩ እንመልከት፦

በክርስትና አስተምህሮ "ዓመተ ምህረት" ማለት የሰው ልጅ በአዳም ኃጢአት ምክንያት እርግማን ላይ ወድቆ ስለነበር፣ ኢየሱስ ተወልዶና በመስቀል ላይ ሞቶ የሰውን ልጅ ኃጢአት ተሸክሞ "ምህረት አወረደ" ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው።

​እስልምና "የአዳም ኃጢአት ለትውልድ ይተላለፋል (Original Sin)" የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል። ቁርኣን በግልጽ "ማንም ነፍስ የሌላዋን ነፍስ ኃጢአት አትሸከምም" ይላል። እያንዳንዱ ሰው ንጹሕ ሆኖ ነው የሚወለደው።

​በእስልምና ምህረት (መግፊራ) የሚገኘው በቀጥታ ወደ አላህ በመጸጸት እንጂ፣ በማንም ነብይ መሰቀልም ሆነ ደም መፍሰስ አይደለም። ዒሳ (ዐ.ሰ) ታላቅ ነብይ እንጂ፣ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ ኃጢአት የተሸከመ አዳኝ አይደለም።

​ስለዚህ አንድ ሙስሊም "ዓመተ ምህረት" ብሎ በሚጽፍበት ወይም በሚናገርበት ጊዜ፣ ይህንን የክርስትናን ሥነ-መለኮት እንደተቀበለ ይቆጠራል። ለዚህ ነው ሙስሊሙ ይህን ቃል መጠቀም በሸሪዓ የማይፈቀድለት።

​መፍትሔው ምንድን ነው?

ሀገር የጋራ ናት። ሀገራዊ አሰራሮችም የሁሉንም ዜጋ እምነት የማያጋጩና ገለልተኛ መሆን አለባቸው።

"ዓ.ል" (ዓመተ ልደት) ብንል፦ ዒሳ (ዐ.ሰ) መወለዱን ስለሚያመለክት፣ የቀኑ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ሀተታውን ባንቀበልም በጥቅሉ ግን ሙስሊሙም ልደቱን ስለሚያምንበት ከማንም እምነት ጋር አይጋጭም።

"እ.ኢ.አ" (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) ብንል፦ አቆጣጠሩን ሃይማኖታዊ ከመሆን አውጥቶ ሀገራዊ እና የጋራ ያደርገዋል።

​የምክር ኮሚሽኑ ያቀረበው ሀሳብ ይህንን ልዩነት ያከበረ፣ ብዝሃነትን ያማከለ እና ማንም በሌላው እምነት ውስጥ ገብቶ እምነቱን እንዳያጎድል የሚጠብቅ የሰለጠነ ሀሳብ ነው። ክርስቲያን ወገኖቻችን በግላቸው፣ በቤተክርስቲያናቸውና በሰነዳቸው "ዓ.ም" ማለታቸውን ማንም አልከለከላቸውም። ነገር ግን በጋራ ሀገራዊ ሰነዶች ላይ የኔን እምነት ትርክት ሙስሊሙም ይጋራው ብሎ ማስገደድ፣ ከፍትህም ሆነ ከአብሮነት ያፈነገጠ ፅንፈኝነት ነው!

ፌስቡክ | ዋትስአፕ
👍90❤25😱2
August 24, 2026 3.7K 1 9