ክርስቲያን ወገኖች "ጅን"ን በተመለከተ ባለው የእስልምና አስተምህሮት ዙሪያ የሚሳለቁት፣ ቃሉን ከራሳቸው የ"ጋኔን" (እርኩስ መንፈስ) ትርጓሜ ጋር በማምታታት ነው። በክርስትና አስተምህሮ ጋኔን ማለት ወደ ንስሐ የማይመለስና የወደቀ እርኩስ መንፈስ ነው። "ታዲያ ከእርኩስ መንፈስ ጋር እንዴት ወንድማማችነት ይፈጠራል?" ብለው መገረማቸው የዚሁ የተሳሳተ መነጽር ውጤት ነው።
እውነታው ግን እጅግ የተለየ ነው። በእስልምና ጅን ማለት ልክ እንደ ሰው ልጅ ነጻ ፍቃድ የተሰጠው፣ የሚያስብ እና የራሱ ምርጫ ያለው ፍጡር ነው። በመሆኑም ከነሱ ውስጥ አላህን የሚያመልኩ ደጋጎች እንዳሉ ሁሉ፣ የሚያምፁ እርኩሳንም (ሰይጣናት) አሉ። እስልምና በእምነት "ወንድሞቻችን" የሚለው እነዚያን ፈጣሪያቸውን አውቀው በጎ መንገድን የመረጡትን አማኝ ጅኖችን እንጂ፣ አጥፊዎቹን አጋንንት አይደለም። ወንድማማችነት የሚገነባው በአምልኮ አንድነት እንጂ፣ በፍጡርነት የዘር ሐረግ አይደለም።
ይህንን ሀሳብ የሚያጣጥሉ ወገኖች፣ ራሳቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቢመዝኑት ተመሳሳይ ሎጂክ ያገኛሉ። በራእይ ዮሐንስ ምዕራፍ 22 ቁጥር 9 ላይ፣ ዮሐንስ ላናገረው መልአክ ሊሰግድለት ሲል፣ መልአኩ እንዲህ ብሎ ገሰጸው፦ "እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር... አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ።"
እዚህ ላይ መሠረታዊ ጥያቄ እናንሳ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአይን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር የሆነውን "መልአክ" የሰው ልጆች "ወንድምና አብሮ ባሪያ" መሆኑን ካረጋገጠ፣ እስልምና ነጻ ፍቃድ ኖሯቸው አላህን የሚያመልኩ መንፈሳዊ ፍጡራንን (አማኝ ጅኖችን) "የእምነት ወንድሞቻችን ናቸው" ሲል ለምን እንግዳ ይሆንባቸዋል? ትምህርቱ እጅግ ግልጽ ነው፤ በፈጣሪ ፊት የየትኛውም ፍጡር ክብርና ዝምድና የሚለካው፣ ለጌታው ባለው ፍጹም ታዛዥነት እንጂ በተፈጠረበት አካል አይደለም! ተውሒድ (አምላክን በብቸኝነት ማምለክ) በሰዎችና በጅኖች መካከል ያለውን ልዩነት አፍርሶ የሚያስተሳስር ታላቅ የወንድማማችነት ዘለበት ነው!
ፌስቡክ | ዋትስአፕ
63
22August 15, 2026 5.3K 14