የሰው ልጅ በተፈጥሮው ስሜታዊ ፍጡር ነው። በዘመናዊው የሥነ-ልቦና እና የፊዚዮሎጂ ሳይንስ እንደተረጋገጠው፣… — የሕያ ኢብኑ ኑህ | Yahya Ibnu Nuhe — TG.ME

የሕያ ኢብኑ ኑህ | Yahya Ibnu NuhePhoto
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ስሜታዊ ፍጡር ነው። በዘመናዊው የሥነ-ልቦና እና የፊዚዮሎጂ ሳይንስ እንደተረጋገጠው፣ በአካል መነካካት በሰውነታችን ውስጥ እንደ "ኦክሲቶሲን" እና "ዶፓሚን" ያሉ የቅርበት እና የስሜት መነሳሳትን የሚፈጥሩ ሆርሞኖች እንዲመረቱ ያደርጋል። ንክኪ በሁለት ሰዎች መካከል ያለውን ሥነ-ልቦናዊ የርቀት ግድግዳ የማፍረስ ከፍተኛ ኃይል አለው።

​እስልምና ይህንን የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ዝንባሌ (ፍትወተ-ሥጋ) በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም ሎጂኩ እጅግ ግልጽ ነው፦ "አንድን አደጋ ለመከላከል፣ ወደ አደጋው የሚያደርሱትን መንገዶች በሙሉ መዝጋት ያስፈልጋል።" አንድ ሰው በሚያዳልጥ ጭቃ ላይ እየተንሸራተተ "አልወድቅም" ብሎ ማሰብ እንደማይችለው ሁሉ፣ የሰውን ልጅ ከተፈጥሯዊ ስሜቱ ጋር እያጋጩ "በንጹህ ልብ ከተደረገ ችግር የለውም" ማለት ምክንያታዊነት የጎደለው የዋህነት ነው። ለዚህም ነው እስልምና መጨባበጥን እንደ አንድ የዝሙት መግቢያ በመቁጠር አስቀድሞ በር የሚዘጋው።

መጽሀፍ ቅዱስ በማቴዎስ ወንጌል፣ ምዕራፍ 5፣ ቁጥር 28 ፦ "ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል"። ይላል። ​እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እናንሳ፤ መጽሐፍ ቅዱስ "ማየት" ብቻውን የልብን ንጽህና አጉድፎ ወደ "ልብ ዝሙት" ያደርሳል ብሎ ካመነ፣ ከእይታ በበለጠ እጅግ ጠንካራ ስሜትን የሚቀሰቅሰው "አካላዊ ንክኪ (መጨባበጥ)" እንዴት "በንጹህ ልብ" በሚል ሰበብ ችላ ሊባል ይችላል? እይታ ኃጢአት ከሆነ፣ መነካካት በሎጂክ ደረጃ የከፋ ነው።

አላህ የሰው ልጅን የፈጠረ ጌታ እንደመሆኑ፣ ለሰው ልጅ የቱ እንደሚበጀው አስቀድሞ በማወቅ መከላከያ አጥርን አበጅቶለታል። እስልምና እጅግ ተግባራዊ (Practical) የሆነ ዲን ነው። በሽታው ከመጣ በኋላ መድኃኒት ከመፈለግ፣ በሽታው የሚመጣበትን መንገድ አስቀድሞ ማድረቅን የሚመርጥ መለኮታዊ ሀይማኖት ነው።

ፌስቡክ | ዋትስአፕ
👍95❤19👏8🔥4
August 14, 2026 4.9K 20