ማክሰኞ:- ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት በድምቀት የተጠናቀቀው የጀነራል ዊንጌት የክረምት እግር ኳስ ውድድር ሻምፒዮን ሆነ!
በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሲካሄድ የቆየው የአሰልጣኞች የክረምት ስፖርታዊ የእግር ኳስ ውድድር እጅግ ማራኪ እና ፉክክር በታከለበት የፍፃሜ ጨዋታ በዛሬው ዕለት በድምቀት ተጠናቋል። በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የዋንጫ ጨዋታ የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንትን ድንቅ ብቃት በማሳየት የዘንድሮው የዋንጫ አሸናፊ መሆን ችሏል።
ለፍፃሜው ደርሰው ዋንጫውን ለማንሳት የተፋለሙት አይሲቲ ዲፓርትመንት (Wingate Best) እና ኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት ያደረጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ነበር። ከጨዋታው በፊት ለዋንጫው ሰፊ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት የአይሲቲ ዲፓርትመንት ተጫዋቾች የጨዋታ የበላይነት በመውሰድ የመጀመሪያውን ግብ ከመረብ ጋር ማዋሃድ ቢችሉም ኮንስትራክሽኖች በአጭር ጊዜ ውስጥ አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ አግኝተዋል።
ከእረፍት መልስም ሁለቱም ቡድኖች በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታ በማሳየት ተጨማሪ ሁለት ሁለት ግቦችን አስቆጥረው መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። አይሲቲዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስደው ወደ ግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የኮንስትራክሽኑን ግብ ጠባቂ ማለፍ እና ኳስ ከመረብ ማገናኘት አልተቻላቸውም።
አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት የኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት ግብ ጠባቂ የሆነው ዘካሪያስ ገብሬ የዕለቱ ኮከብ በመሆን አድምቋል! ዘካሪያስ ሁለት የአይሲቲ ቅጣት ምቶችን ድንቅ በሆነ ብቃት አምክኖ ቡድኑን ታድጓል። አይሲቲዎች በበኩላቸው የተሰጣቸውን ኳሶች መከላከል ባለመቻላቸው ኮንስትራክሽን ዲፓርትመንት በ2 የግብ ልዩነት በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።
ከዋንጫው ጨዋታ አስቀድሞ የደረጃ ፍልሚያ የተካሄደ ሲሆን ጀነራል መካኒክስ /GM/ (Iron Man) ከአግሮ ቢዝነስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጀነራል መካኒክስ ተጋጣሚውን 6 ለ 2 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የ3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በውድድሩ መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁት ዲፓርትመንቶች ደማቅ የሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ተካሂዶ የዘንድሮው የክረምት እግር ኳስ ውድድር በስኬት ተጠናቋል።
"በላቀ አገልግሎት የመረጃ ተደራሽነት"
32
3
1August 4, 2026 6.7K 5