ሥልጣን የክብር መለኪያ ሳይሆን ከባድ አደራ እና መስዋዕትነት ነው!
በዓለም ታሪክ ማህደር ውስጥ ከዕውቀት፣ ከፍትሕ እና ከከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት አንፃር እጅግ የነነ ስም ያለው የፖለቲካ እና የሞራል ምሽግ የሆነው የሁለተኛው ኸሊፋ የዑመር ኢብኑ አል-ኸጣብ አስተዳደራዊ ፍልስፍና በቁርኣናዊ እሴቶች እና በሰላ ትችት ላይ የተመሠረተ የዕለት ተዕለት ልምምድ ነበር። ግዛቱ እየሰፋ ሲሄድ ከስሜታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ ወጥቶ ሰፊውን ግዛት በዘላቂ ተቋማት ለማዋቀር ሠርተዋል። የዜጎችን መብት፣ የጡረታ አበል እና የገንዘብ ዝውውር በሥርዓት የሚመዘግብበትን የመንግሥት ግምጃ ቤት በመዘርጋት ግልጽነት ያለው የፋይናንስ አስተዳደር ሰፍኗል። ዳኛውን ከመንግሥት አስፈፃሚ አካል በመነጠል የሰጡት የፍትሕ ነፃነት እና ገለልተኝነት ዛሬም ድረስ የዓለም የሕግ ልህቀት መሠረት ሆኖ ይጠቀሳል።
በሰው ኃይል አስተዳደር እና በሹመት ምርጫ ሂደት ውስጥ የዘመድ አዝማድ ፖለቲካን በመሻር ብቃትን እና ታማኝነትን ብቻ መሠረት አድርገዋል። ለአንድ የሥራ መደብ ብቁ የሆነውን ሰው መምረጥ በሃይማኖታዊ እና በሞራል ግዴታ ልክ የሚታይ መሆኑን በማመን ከብቃት ውጭ የሆነ ሹመት በሕዝብ ላይ የሚፈጸም ክህደት መሆኑን አስመስክረዋል። በብቸኝነት ከመወሰን ይልቅ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራንን እና አዋቂዎችን ሰብስቦ ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ ባለቤትነትን የሚፈጥር ሰፊ የምክር ባህልን አጽንተዋል።
መሪ ማለት የሕዝብ አገልጋይ እንጂ ገዥ አለመሆኑን በተግባር አሳይተዋል። በሌሊት እየተዘዋወሩ የዜጎችን ድምፅ፣ ችግር እና የኑሮ ሁኔታ በግል ማረጋገጥ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነበር። አንዲት በግ ብትጎዳ ወይም ብትጠፋ እንኳን በዕለተ ትንሣኤ እንደሚጠየቁበት በመሰጋት የገዛ ራሳቸውን ኃላፊነት ከሥነ-ምግባር እና ከሕዝብ ደህንነት ጋር አቆራኝተውታል። በረሃብ እና በድርቅ ወቅት ያሳየው የድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ከሌሎች ግዛቶች የእርዳታ አቅርቦት ሰንሰለት በመዘርጋት ሕዝቡን ከከፍተኛ ውድቀት አድነዋል። የተማረከውን መሬት ለተዋጊዎች በምርኮ መልክ ከመከፋፈል ይልቅ የሕዝብ ሀብት አድርጎ በማቆየት ከሚገኘው ገቢ የሀገር አቀፍ የልማት በጀት እና የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጥበትን ዘላቂ ስልት ነድፈዋል።
በታላቅ ግዛት ላይ ተሹኡመው ሳለ በራሳቸው ላይ ጥብቅ የሞራል ዲሲፕሊን በመጫን በድህነት በመኖር እና ለሕዝብ ጥቅም ሲሉ ከራስ ጥቅም በመላቀቅ የትኛውንም ሥልጣን በክብር እና በጽናት ማስተዳደር እንደሚቻል አሳይተዋል። ሕይወታቸው ከእውነት እና ከግልጽ ተጠያቂነት ጋር የተጣጣመ በመሆኑ ሥልጣን የክብር መለኪያ ሳይሆን የከበደ አደራ እና የሕዝብ አገልጋይነት መስዋዕትነት መሆኑን አጽንተዋል።
በመሆኑም የዚህ ታላቅ መሪ የዕድሜ ልክ ጉዞ በቁሳዊ ድል ላይ ብቻ ሳይሆን በፍትሕ፣ በሰብአዊ ክብር እና በተቋማዊ ጽናት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ምን ይመስል እንደነበር በግልጽ ያሳያል። የትኛውም ማህበረሰብ ሊያድግ የሚችለው ሕዝባዊ አደራ ሲከበር እና መሪዎች ለህዝባቸው ታማኝ ሲሆኑ ብቻ ነው።
ዛዲግ አብርሀ
የአፍሌክስ ፕሬዝደንት






