+ የበረሃው መናኝ + መጥምቁ ዮሐንስ በሕፃንነቱ የመነነ የምድረ በዳ ሰው ነበር፡፡ የቀን ሐሩሩን የሌሊት ቁሩን ታግሦ በማይመቸው በረሃ ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ የምድረ በዳው ሰው የዮሐንስ ድምፅ ታዲያ ከአይሁድ ሸንጎ እስከ ሔሮድስ ቤተ መንግሥት ድረስ ዘልቆ ይሰማ ነበረ፡፡ የምናኔን ኃይል ተመልከቱ! በምድረ በዳ ለመኖር የጨከነ ባሕታዊ ድምፅ ግርማው በከተማ ይሰማል፡፡ እርሱ በዋሻ ውስጥ እያደረ በቤተ መንግሥት በምቾት አልጋ የሚያድሩትን ሰዎች ያንቀጠቅጥ ነበር፡፡ ‘ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር’ (ማቴ. 3፡3) መናኙ ዮሐንስ ለስብከት ወደ ከተማ መምጣት አላስፈለገውም፡፡ ሕዝቡ ‘ወደ እርሱ ይወጡ ነበር’ ባሕታዊ ዮሐንስ ምድረ በዳውን አልለቀቀም፡፡ ሕዝቡን ለማምጣትም ወደ ሕዝቡ ገብቶ አብሮ መኖር አላስፈለገውም፡፡ ሕዝቡ ለነፍሳቸው ዕረፍት ፍለጋ ወደ ዮሐንስ ይሔዱ ነበር፡፡ ወደ ዮሐንስ ያልሔደ ማን አለ? ወታደሩ ፣ ባለ ሥልጣኑ ፣ ፈሪሳውያኑ ፣ ሰዱቃውያኑ ሁሉ ከሚመጣው ቁጣ ሊሸሹ ወደ ዮሐንስ ይመጡ ነበር፡፡ እውነተኛው መናኝ ዮሐንስ ሰዎችን ፈልጎ ወደ ዓለም የሚመጣ ሳይሆን ዓለማውያኑ ፈልገውት ወደ እርሱ የሚሔዱለት ነበር፡፡ አባ መቃርስን አባ እንጦንስን ፈልገው ወደ አስቄጥስ በረሃ ሰዎች እንደገሰገሱ ፣ አባ ሳሙኤልን ፈልገው ወደ ዋልድባ እንደተጓዙ ፣ አባ አረጋዊን ብለው ወደ ደብረ ዳሞ እንደገሰገሱ ሰዎች የዮሐንስን ፈለግ የተከተሉ የምድረ በዳ መናኞች ዓለምን ወደ እነርሱ ይስባሉ እንጂ እነርሱ በዓለም አይሳቡም፡፡ ዮሐንስ ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ፣ ልብሱ የግመል ጠጉር ነበረ፡፡ ሰውነት የሚኮሰኩስ ቆዳን የሚረብሽ ልብስ ለብሶ ነበር፡፡ የግመል ጠጉር ዕርቃንን ከመሸፈኑ ውጪ ለብርድም ለሙቀትም የማይመች ዓይነት ልብስ ነበር፡፡ ዮሐንስን በሕይወቱ ከሚመስለው ከኤልያስ በስተቀር እንዲህ ዓይነቱን ልብስ ሊለብሰው የሚወድ ሰው አልነበረም፡፡ ጌታ ወደ ዮሐንስ የመጡትን ሰዎች ‘ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀኝን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታቱ ቤት አሉ’ ብሎ ነበር፡፡ ማቴ. 11፡8 እውነት ነው ዮሐንስ አለባበሱን ለማየት የሚጓጓለት ሰው አልነበረም፡፡ ምን ዓይነት ልብስ ለብሶ ይሆን ብላችሁ ልታዩ ከመጣችሁ የሚያምር ልብስ የሚለብሱት ሰዎች ያሉት በነገሥታቱ ቤት ነው፡፡ ዮሐንስ ልብሱ የግመል ጠጉር ነው፡፡ የግመል ጠጉር ሰውነት ይኮሰኩሳል:: ለልብስነት አይመችም ለአገልግሎት ግን ይመቻል:: ልብስህ ግመል ምግብህ አንበጣ ቤትህ ምድረ በዳ ከሆነ ያለሃሳብ ታገለግላለህ:: እንደ በረሃው መናኝ እንደ ምድረ በዳው ባሕታዊ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ቤቴ ሚስቴ ድስቴ ልብሴ ምግቤ ሳትል ዝም ብለህ ለጌታህ መንገድ ትጠርጋለህ:: የማታጥበው የማትተኩሰው የግመል ጠጉር ከለበስህ ቃሉን ከመስበክ በቀር ምን ያሳስብሃል? ዮሐንስ የስብከቱ ኃይል ምድርን ያንቀጠቀጠውም ለዚህ ነው፡፡ ነገሥታቱን ለመገሠፅ ያልከበደውም ለዚህ ነው፡፡ ምን አጣለሁ ብሎ ይፈራል? ምን እበላለሁ እንዳይል ቀድሞውንም ምግቡ አንበጣ ነው፡፡ ምን እለብሳለሁ? ብሎ እንዳይሰጋ የሚለብሰው የግመል ጠጉር ነው፡፡ ሰውነቱን ምቾት ስላላስለመደ ዮሐንስ እንዳያጣው የሚፈራው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ቤቴን እንዳይቀሙኝ ብሎ እንዳይፈራም እርሱ የምድረ በዳ መናኝ ነው፡፡ ባሕታዊው ዮሐንስ ሆይ ያማረ በፍታና ቀጭን ልብስ የለበስን ፣ ያማረ የምንበላ የምንጠጣ ፣ ባማረ አልጋ የምንተኛ ሰባኪያን አንተ መንገድ የጠረግህለትን ጌታ መንገድ ስንዘጋበት ስታይ ምንኛ ትታዘበን ይሆን? ሔሮድስ ከሔሮድያዳ ቢጋባና ቢወልድ ትንፍሽ የማንል ይልቁንም ሰርጉን ለመባረክ የምንሮጠው ለምን ይመስልሃል? ሔሮድስ እንኳን እናቲቱን ልጅትዋንም ጨምሮ ቢያገባ ሰምተን እንዳልሰማ የምንሆነው ልብሳችን እንዳንተ የግመል ጠጉር ፤ ምግባችንም የበረሃ አንበጣ ስላልሆነ ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ ሆይ ዛሬ "ለጌታ መንገድ አቅኑ ተራራው ዝቅ ይበል" ልትለን የሚገባህ የሐዲስ ኪዳን ፈሪሳውያንን በዝተናል:: በክርስቶስ የምናምን ሰዱቃውያንን የሔሮድስ ሰርግ ደጋሾች የሔሮድያዳ ጠጅ አሳላፊዎች እልፍ አእላፋት ሆነናል:: በልደትህ ቀን ወደ እኛ ተመልከት:: እኛ እንዳንተ "ዳዕሙ ከመ ያእምርዎ እስራኤል" (እስራኤል ያውቁት ዘንድ ነው) ማለት የምንችል አይደለንምና የምድረ በዳው መናኝ ሆይ ጌታህን እኛ እንድናውቀው አድርገን:: ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ሰኔ 30 2015 ዓ.ም. የመናኙን ምልጃ ለመማጸን የተጻፈ ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን አጥብቃችሁ ስለ እኔ ጸልዩልኝ! በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ [ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ] ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)
85
54