የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን አስቀድሞ ከተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ማዛወር፣ ተቀብሎ ማስተማር በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ - ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በቀን 06/11/2018 ዓ.ም ተፈርሞ ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተላከ ሰርኩላር፤ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ ፈተና ተፈትነው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በሚኒስቴር መ/ቤቱ በመደበኛ እና በሪሚዲያል ፕሮግራም ለዩኒቨርሲቲዎች የሚመደብ መሆኑን አስታውሷል፡፡ ይሁን እንጂ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተመደቡ ተማሪዎች በየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ያሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ጥናት፣ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ዕውቅና ውጪ ዩኒቨርሲቲዎች ባልተሰጣቸው ስልጣንና አግባብነት በሌለው ሁኔታ ተማሪዎችን ከተመደቡበት ውጭ የመቀያየር ሥራ እነደሚሠሩ አረጋግጧል፡፡ ይህም ህብረ-ብሄራዊነትን የሚጉዳና የእኩልነት መብትንና ፍትሃዊ አሠራርን የሚፃረር ሆኖ እንደተገኘ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በመሆኑም በትምህርት ሚኒስቴር ምደባ የተሰጣቸውን የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕውቅና ውጪ በምንም አይነት ሁኔታ አስቀድሞ ከተመደቡበት ማዛወርም ሆነ በማንኛውም ሁኔታ ተቀብሎ ማስተማር በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል፡፡ ይህን ውሳኔ ጥሶ የተገኘ የዩኒቨርሲቲ አመራር ተጠያቂ እንደሚሆኑም ሚኒሰቴሩ አስገንዝቧል፡፡ ✤Join us https://t.me/mock_news https://t.me/mock_news
5
1