ለግብር ከፋዮች በሙሉ፦ ስለ አዲሱ የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ አዋጅ (ቁጥር 1434/2018) ማወቅ የሚገቡዎት… — Ministry of Revenues -Medium Taxpayers Branch No2 — TG.ME

📣 ለግብር ከፋዮች በሙሉ፦ ስለ አዲሱ የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ አዋጅ (ቁጥር 1434/2018) ማወቅ የሚገቡዎት ዋና ዋና ነጥቦች! 📣
የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1434/2018 ከሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም (July 30, 2026) ጀምሮ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ፀድቋል። አዋጁ የታክስ አሰራሩን ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ለማድረግ በርካታ አዳዲስ መብቶችና ግዴታዎችን ይዞ ወጥቷል።
እነዚህን ዋና ዋና ለውጦች በአጭሩ ይወቁ፦
🔹 1. የታክስ አለመግባባትን በስምምነት (Conciliation) የመፍታት መብት
ከታክስ ባለስልጣኑ ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ፣ ጉዳዩን በገለልተኛ አካል አመቻችነት በስምምነት/በዕርቅ መጨረስ ይቻላል።
አሰራሩ ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት እና በሚስጥራዊነት ላይ የተመሰረተ ነው።
ልዩ ዕድል፦ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ይግባኝ ብለው ክርክር ላይ ያሉ ግብር ከፋዮች፣ ጉዳያቸው በዕርቅ እንዲያልቅ አዋጁ ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ በ60 ቀናት ውስጥ ማመልከቻ ማቅረብ ይችላሉ።
🔹 2. በሁኔታ ላይ የተመሰረተ የታክስ ምስክር ወረቀት (Conditional Tax Clearance)
የታክስ ዕዳ ያለበት ግብር ከፋይ በቅሬታ/ይግባኝ ሂደት ላይ ከሆነ ወይም የክፍያ ስምምነት (Installment Agreement) ከፈጸመ፣ በሁኔታ ላይ የተመሰረተ ክሊራንስ ማግኘት ይችላል።
ጥቅሙ፦ የንግድ/የሙያ ፈቃድ ለማደስ፣ በጨረታ ለመሳተፍ፣ የተሽከርካሪ/ማሽነሪ ምርመራ ለማድረግ እና የባንክ ብድር ለማግኘት ያገለግላል።
🔹 3. የታክስ ውሳኔ ማስታወቂያ ማስተካከያ እና ይርጋ
ስህተትን ማረም፦ በታክስ ውሳኔ ላይ የሂሳብ/የስሌት ስህተት፣ አዲስ ማስረጃ ወይም የህግ ትርጉም ግድፈት ካለ ባለስልጣኑ ወይም በግብር ከፋዩ ጥያቄ ውሳኔው ሊስተካከል ይችላል።
የይርጋ ጊዜ፦ በመደበኛ ሁኔታ የራስ ታክስ ስሌት ከቀረበበት ወይም ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ የ5 ዓመት የይርጋ ጊዜ አለው። የታክስ ማጭበርበር ከተረጋገጠ ግን የይርጋ ጊዜው ወደ 10 ዓመት ከፍ ይላል።
🔹 4. ደረሰኝ አለመስጠት እና አስተዳደራዊ ቅጣቶች
ደረሰኝ አለመስጠት፦ ደረሰኝ ሳይሰጥ በሚቀርብበት በእያንዳንዱ ግብይት ላይ 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር አስተዳደራዊ ቅጣት ይጣላል። ይህ ቅጣት በባለስልጣኑ ሊነሳ አይችልም።
የወንጀል ተጠያቂነት፦ ደረሰኝ አለመስጠት ወደ ወንጀል ክስ የሚቀየረው በአንድ የግብር ዘመን ውስጥ ለሁለት ጊዜያት ያህል አስተዳደራዊ ቅጣት ከተቀጡ በኋላ ድርጊቱ ለ3ኛ ጊዜ ከተፈጸመ ብቻ ነው።
የሃሰት ደረሰኝ/ዋጋ ማሳነስ፦ በአንድ ግብይት ላይ ተመሳሳይ ደረሰኝ ላይ የተለያዩ ዋጋዎችን በመመዝገብ ዋጋ ማሳነስ 100,000 ብር ቅጣት እና ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ያስቀጣል።
🔹 5. የድርጅቶች እና የኃላፊዎች ተጠያቂነት
በድርጅት ደረጃ የታክስ ጥሰት ሲፈጸም፣ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይም የፋይናንስ ኃላፊ ተጠያቂ ይሆናሉ።
ነገር ግን ድርጊቱ ከእውቀታቸው ውጭ መሆኑን፣ ያላዘዙ/ያልተባበሩ መሆኑን ወይም መከላከል የሚያስችል የውስጥ ቁጥጥር ስርዓት የዘረጉ መሆኑን ካስረዱ ነፃ ይሆናሉ።
📍 ተጨማሪ መረጃ፦ የደንበኞች ቻርተርን፣ የኤሌክትሮኒክስ ደረሰኝና የQR ኮድ አጠቃቀም መመሪያዎችን በመከተል የግብር ግዴታዎን በወቅቱ ይወጡ፤ ህጋዊ አሰራርን በመከተል ንግድዎን ያሳድጉ!
❤22
August 21, 2026 8.5K 3 135