20 ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ።
በስምንት ዓመት የትግበራ ሂደት 20 ሚሊየን ወጣቶችን በልቦና ውቅር አሰልጥኖ ለማብቃት ያለመ የለውጥ ትውልድ ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድና የብሬክስሩ ትሬዲንግ ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ ሁሴን ተፈራርመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት:-እንደ ሀገር ለውጥ ለማምጣት ወጣቶች የልቦና ውቅራቸው በሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር የተዋቀረ ሊሆን ይገባል።
መንግስት ሁሉን አቀፍ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ በተለይም ወጣቶች በመልካም ስብዕና የታነጹ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የለውጥ ትውልድ ፕሮጀክት 20 ሚሊየን ወጣቶችን አሰልጥኖ ለማብቃት ያለመ መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ለስምንት ዓመት የትግበራ ሂደት ያለው በመሆኑ በ10 ሺህ አሰልጣኞች ስልጠና የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸዋል።
የብሬክስሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነጻነት ዘነበ በበኩላቸው፤ የለውጥ ትውልድ ፕሮጀክት ዓላማ ባለራዕይ ቅን አጋዥ ብቃት ያለውና ባለጸጋ ትውልድ ለሀገር ማፍራት ነው።
ፕሮጀክቱ በ2023 ዓ.ም 20 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሰልጠን 2 ሚሊየን የተለወጡ ወጣቶችን በማፍራት አንድ ሚሊየን የሥራ እድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ስልጠናው በመጀመሪያው ዓመት በ13 ከተሞች ላይ ለ10 ሺህ ወጣቶች እንደሚሰጥ ገልጸው ፕሮጀክቱ ወጣቱ ለራሳቸው ዋጋ እንዲሰጡ በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ በማድረግ ሰርቶ መለወጥ የሚችል ወጣት ለማፍራት እንደሚያስችል አስረድተዋል። #ኢፕድ
Share share
5
1February 29, 2024 2.3K 1 3