የግፍ እስረኞቹ ጥቃት ተፈጸመባቸው አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥቃት… — አንድ እርምጃ — TG.ME

የግፍ እስረኞቹ ጥቃት ተፈጸመባቸው አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያሌው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጥቃት ተፈፀመባቸው። ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ/ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እስረኞች ወደ ማደሪያቸው ከገቡ በኋላ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ላይ ቀይ ቦኔት የጫኑ የፌደራል ፖሊሶች ቁልፍ ሰብረው ገብተው አቶ ክርስቲያን ታደለን እና አቶ ዮሐንስ ቧያሌውን ከእስር ቤታቸው እንዳስወጧቸው እና እስከ ሌሊቱ 7:00 ሰዓት ድረስ ሜዳ ላይ አስተኝተው እንዳሳደሯቸው ተገልጿል። በተመሳሳይ ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ ፕሮፌሰር መዓረጉ ቢያበይን እና ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ይሄው ድርጊት የተፈፀመባቸው መሆኑን አርብ ሚያዚያ 24 ቀን 2017 ዓ/ም ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።  "ቀይ ቦኔት የጫኑ የፌደራል ፖሊሶች ምሽት 12:00 ሰዓት  በሩን በኃይል ከፍተው ከገቡ በኋላ ሁላችንንም እጃችንን ወደ ላይ እንድናደርግ አዘው ሜዳ ላይ በሰልፍ አቁመውን በመሳሪያ ሲያስፈራሩን ነው ያደሩት" ሲሉ ነው ለፍርድ ቤቱ የገለፁት። "ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ድብደባ የፈፀሙብን የመንግስት ሹማምንት ከሁለት ዓመት በኋላ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን አጥር ጥሰው፣ የተኛንበትን ቤት በር በኃይል ሰብረው እስከ ሌሊት 7:00 ሰዓት ድረስ  ሜዳ ላይ አሰልፈው አሳድረውናል። ሕይዎታችን አደጋ ላይ መሆኑን  ሕዝባችን እንዲያውቅልን" ሲሉ አሳስበዋል። አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ ከአንድ አመት በፊት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት የከፋ የጤና መታወክ ገጥሟቸው እንደ ነበር ይታወቃል። በመሆኑም ጤናቸው ገና ሳያገግም በድጋሜ ሜዳ ላይ ተሰልፈው እንዲያድሩ መደረጉ ለባሰ የጤና እክል ተጋልጠዋል ተብለዋል። የፌደራል ፖሊሶች የማረሚያ ቤቱን አጥር ሰብረው ለምን እንደገቡ እና በሽብር የተጠረጠሩ እስረኞችን ለምን ከክፍላቸው አስወጥተው ሜዳ ላይ እንዳሳደሯቸው የታወቀ ነገር የለም ሲል መሰረት ሚዲያ ዘግቧል።

May 3, 2025 216