Diinii kee Anaakara (Md Ali): post #4679 — TG.ME

የሰዎች ህይወት እና ንብረት በሌላው ላይ ሐራም ነው!
~
ከአቡ በክረህ (አላህ ይውደድላቸው) ተይዞ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

" إِنَّ دِمَاءَكُمْ وَأَمْوَالَكُمْ وَأَعْرَاضَكُمْ بَيْنَكُمْ حَرَامٌ كَحُرْمَةِ يَوْمِكُمْ هَذَا، فِي شَهْرِكُمْ هَذَا، فِي بَلَدِكُمْ هَذَا "
“ደማችሁ (ሕይወታችሁ)፣ ንብረታችሁ እና ክብራችሁ በእናንተ ላይ እርም (የተከለከለ) ነው፤ ልክ በዚህ ወራችሁ እና በዚህ አገራችሁ ውስጥ ይሄ ቀናችሁ እንዳለው ክብር።”

[ቡኻሪይ (39) ከዘገቡት ሐዲሥ የተወሰደ ነው። ሙስሊምም (2816) ዘግበውታል።]

* ቡኻሪይ (7078) ውስጥ በሚገኝ ሌላ ዘገባ ደግሞ እንዲህ የሚል አለ፦
" وَأَبْشَارَكُمْ، عَلَيْكُمْ حَرَامٌ كَحُرْمَةِ يَوْمِكُمْ هَذَا "
“አካሎቻችሁም እንዲሁ እንደዚህ ቀናችሁ ክብር የተከበሩ ናቸው።”

* በተጨማሪም ነብያችን ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
" لَا تَرْجِعُوا بَعْدِي كُفَّارًا، يَضْرِبُ بَعْضُكُمْ رِقَابَ بَعْضٍ "
“ከኔ በኋላ ከፊላችሁ የከፊሉ አንገት የሚሰይፍ ከሃዲዎች ሆናችሁ አትመለሱ።” [ቡኻሪይ (67 እና 7078] እና ሙስሊም (1679) ዘግበውታል።]

የቃላት መፍቻ፦
=
1. “ይሄ ቀናችሁ” የተባለው ዙልሒጃ አስር ሲሆን የዒደል አድሓ የመጀመሪያው ቀን ነው።
2. “በዚህ ወራችሁ” የተባለው የተከበረው የዙልሒጃ ወር ነው።
3. “በዚህ ሃገራችሁ” የተባለው የተከበረው የአላህ ቤት፣ የተከበረችዋ መካ ለማለት ነው።

ከሐዲሡ የሚወሰዱ ትምህርቶች፦
=
1. የሙስሊሞች ደም ፈፅሞ ሊደፈር የማይገባው እርም እንዲሁም በጣም የተከበረ እንደሆነ፣
2. የሰዎችን ንብረትና ክብር መዳፈር ክልክል እንደሆነ እና
3. የሙስሊም ደሙ፣ ንብረቱ እና ክብሩ ከተከበረው ሃገር፣ ከተከበረው ወር እና ከተከበረው ቀን ክብር በላይ እንደሆነ እንወስዳለን።

ዐብዱላህ ብኑ ዐምር ብኒል ዓስ (አላህ ይውደድላቸው) ባስተላለፉት ሐዲሥ የአላህ መልዕክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦

" وَالَّذِي نَفْسِي بِيَدِهِ لَقَتْلُ مُؤْمِنٍ أَعْظَمُ عِنْدَ اللهِ مِنْ ‌زَوَالِ ‌الدُّنْيَا "
“ነፍሴ በእጁ በሆነችው (ጌታዬ) እምላለሁ! አንድን አማኝ መግደል አላህ ዘንድ ከድፍን ዓለም መጥፋት የከፋ ነው።” [ነሳኢይ (3986) ዘግበውታል።]

* ሙስሊም ያልሆኑ አካላትም እንዲሁ ሊበደሉ አይገባም። ይህንን የሚመለከት ማስረጃ ሌላ ጊዜ አቀርባለሁ፣ ኢንሻአላህ።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor
https://t.me/IbnuMunewor
August 17, 2026 153